addisnews

I'm standing for real freedom. I regard freedom of expression as the primary right without which one can not have a proper functioning democracy.

በአንበሳ የሞት አደጋ የደረሰባቸው አቶ አበራ ሲሳይ የመጨረሻ ደቂቃዎች

vc
ቀነኒሳ ወርቁ በተባለ አንበሳ የተገደሉት ጐልማሳ የቀብር ሥነ ሥርዓት ተፈጸመ

ባለፈው ሰኞ መስከረም 6 ቀን 2005 ዓ.ም. ከማለዳው 1፡35 ሰዓት ላይ ስድስት ኪሎ በሚገኘው አንበሳ ግቢ የፅዳት ሥራ ሲያከናውኑ ቀነኒሳ ወርቁ በተባለ አንበሳ የሞት አደጋ የደረሰባቸው አቶ አበራ ሲሳይ፣ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው በገርጂ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በበነጋታው ከቀኑ በስድስት ሰዓት ላይ ተፈጸመ፡፡

በዕለቱ በግቢው ውስጥ ሌላ ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩትና አናብስቱን የሚመግቡት አቶ ምትኩ ጪብሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አደጋው የደረሰው አቶ አበራ የፅዳት ሥራቸውን እያከናወኑ በነበረበት ወቅት በተፈጠረ መዘናጋት ነው፡፡

ሟች ቀነኒሳ የሚባለው አንበሳ የሚገኝበትን ቁጥር አሥር ዋሻ ከከፈቱና ከማደርያው ወደ መዋያው ሥፍራ ካስወጡት በኋላ፣ መዝጋት የነበረባቸውን በር ሳይዘጉት በመቅረታቸውና ተዘናግተው ወደ ክፍሉ በመግባታቸው፣ ከአንበሳው ጋር በተፈጠረው ትንቅንቅ ሕይወታቸው ማለፉን አክለው ገልጸዋል፡፡

ሟች ሁሉንም ሥራቸውን ሠርተው ጨርሰው እንደነበር ያስታወሱት አቶ ምትኩ፣ “ከአንበሳው ጋር ሊጋፈጥ የቻለው የዘጋ የመሰለውን በር ባመለዝጋቱ ነው፡፡ በዚህም ከአንበሳው ጋር ፊት ለፊት ተገናኙ፤” በማለት አስረድተዋል፡፡

አቶ ምትኩ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አንበሳው አቶ አበራን ማጅራታቸውን ይዞ ከ15 እስከ 20 ለሚሆኑ ደቂቃዎች ቆይቷል፡፡ በዚህም ምክንያት በሟች ላይ መንገላታት መድረሱን አብራርተዋል፡፡ አንበሳው ሟችን ማጅራታቸው አካባቢ ነክሶ በመያዝ በማደርያውና በመዋያው ክፍሎቹ እየተመላለሰና በእጆቹም ከፍና ዝቅ እያደረገ ያንገላታቸው እንደነበር ገልጸዋል፡፡

“አደጋው በደረሰበት ወቅት በርከት ያልን ሰዎች ለማስለቀቅ የተለያየ ጥረት ያደረግን ቢሆንም፣ አንበሳው ግን ሟችን በጥርሱ ነክሶ ወደኔ በተደጋጋሚ በመጠጋት ያስፈራራኝ ነበር፤” በማለት አቶ ምትኩ አስረድተዋል፡፡ አንበሳው ሟችን ከመጣልና ከማንሳት ባለፈ በጥርሱ እየጐተተ ወዲያና ወዲህ ያመላልሳቸው እንደነበር፣ ሟችም ለተወሰኑ ደቂቃዎች የድረሱልኝ ጥሪዎች ካሰሙ በኋላ ሕይወታቸው አለፈ በማለት አሰቃቂውን አደጋ ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ ዘግይተው ወደ ሥራ እንደገቡ የገለጹት የአዲስ ፓርክ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሴ ክፍሎም ሥራው ምንም ዓይነት መዘናጋት ሊኖርበት እንደማይገባ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ “ከአንበሳ ጋር ለሰከንድ ከተዘናጋህ ሕይወትህን ታጣለህ፤” በማለት የሥራውን ክብደትና አስቸጋሪነት አስረድተዋል፡፡ እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ ባልደረባቸውን ለማዳን ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡ ፖሊስም ደርሶ ነበር፡፡ “ጥይት ወደ ሰማይ ከመተኮስ ባሻገር የባልደረባችንን ሕይወት ለመታደግ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ ነገር ግን አያያዙን ስታየው በቀጥታ አንበሳውን በመጉዳት ባልደረባችንን ለማዳን መሞከር የባሰ ማስቦጨቅና ሌላ ችግር ውስጥ መክተት ነው፤” ብለዋል፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ አንበሳው ፊቱን በሟች ሸፍኖ ከወዲያ ወዲህ ይመላለስ ስለነበር ይህንን ማድረግ አልተቻለም በማለት አክለዋል፡፡

ማደንዘዣዎችንና የመሳሰሉ ሌሎች የጥንቃቄ ዘዴዎችን መጠቀም ይችሉ እንደነበር ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ኃላፊው ሲመልሱ፣ ሐኪሙ የሚገባው ጠዋት 2፡30 ሰዓት ላይ ስለሆነ እንዲህ ዓይነት ነገሮችን ያጋጥማሉ በሚል የተደረገ ዝግጅት የለም ብለዋል፡፡ የአናብስቱ መኖርያ ሥፍራ ፅዳት የሚከናወነው ከንጋቱ 11 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት ነው፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያት ያቀረቡት ደግሞ በፓርኩ ከምሥረታው ከ1940 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲህ ያለ ነገር አለመኖሩን ነው፡፡ ድንገት እንዲህ ያለ ነገር ቢከሰት ተብሎ የተደረገ ልዩ ቅድመ ጥንቃቄ ግን የለም በማለት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት እዚሁ አንበሳ ግቢ ውስጥ ሌላ አንበሳ መጋቢውን መግደሉ አይዘነጋም፡፡

አንበሳ ግቢ በአሁኑ ወቅት 15 አናብስት ሲኖሩት፣ ከእነዚህ ውስጥ ስምንቱ ወንድ ሲሆኑ ሰባቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡ ከነዚህም መካከል የአምስቱ አናብስት ስም በታዋቂ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ስም የተሰየመ ነው፡፡ የአንበሳ ግቢ ፓርክ በ1940 ዓ.ም. በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ነው የተመሠረተው፡፡ በወቅቱ ወደ ፓርኩ የገቡት ሁለት ጥንድና ሦስት ደቦሎች ነበሩ (ሞላና ሉሉ ከነሚስቶቻቸው እና ሦስት ደበሎች)፡፡ እነዚህ አናብስትም የመጡት ከወለጋ፣ ከኢሉአባቦራ (ጎሬ) እና ሲዳሞ ነው፡፡ አቶ አበራ ለማ ላይ የሞት አደጋ ያደረሰው ቀነኒሳ ወርቁ በፓርኩ ውስጥ ነሐሴ 1 ቀን 1998 ዓ.ም. መወለዱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

አንበሳው ከዚህ ቀደም ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ከተባለ ሌላ አንበሳ ጋር በተደጋጋሚ ይደባደብ ስለነበር፣ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ የተባለው አንበሳ ወደ ሌላ ሥፍራ መዘዋወሩን ዶ/ር ሙሴ ገልጸዋል፡፡

ሟች አቶ አበራ ሲሳይ የ52 ዓመት ጐልማሳና ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት ነበሩ፡፡

ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን።

source: sodere.com

Advertisements

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: