addisnews

I'm standing for real freedom. I regard freedom of expression as the primary right without which one can not have a proper functioning democracy.

ወቅታዊ ችግሮቻችን የራሳችን መንግሥት ባለቤቶች እንድንሆን ይበልጥ ሊያበረቱን ይገባል!

33
በወያኔ አረመኔያዊ አገዛዝ ሳቢያ ከሀገራቸውና ከትውልድ ቀያቸው ተፈናቅለው በዐረቡ ዓለም በተለይም በሳዑዲ ዐረቢያ በሚገኙ ዜጎቻችን ላይ ሰሞኑን እየደረሰ የሚገኘውን ዘግናኝ ሰቆቃና ግድያ በመሪር ስሜትና በንቃት እየተከታልን ነው። አበው “ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳው አይቀበለውም” እንዲሉ እነዚህ ወገኖቻችን በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ‹የሀገራቸው መንግሥት ነው› የሚባልለት የወያኔው መንግሥት እንኳንስ በባዕድ ሀገር በሚገዛው ሀገርም ውስጥ የሚያካሂደውን የመብት ገፈፋና ሕዝቤ በሚለው ዜጋ ላይ በዘር እየከፋፈለ የሚያራምደውን የግፍ አገዛዝ ዐረቦቹም ሆኑ ቀሪው ዓለም ያውቁታል። በመሆኑም ለነዚህ ምሥኪን ዜጎች የሚጮኽላቸውም ሆነ ለመብታቸው መከበር የሚቆረቆርላቸው አንድም መንግሥታዊ አካል እንደሌለ ከበፊት የተገነዘቡት እውነታ ነው። በወገኖቻችን ላይ ይህን ሁሉ ሰማይና ምድር የማይችሉት የግፍ ቁልል እነዚህ የዐረብ መንግሥታት የፀጥታ ኃይሎች ሲከምሩባቸው ማንም ዝምባቸውን እሽ የሚል ወይም ጠንከር ባሉ ቃላት እንኳን ተቃውሞ የሚያቀርብ አካል እንደማይር ያውቃሉ። ለዚህም ነው ታላላቅ የሚዲያ አውታሮች ሳይቀሩ ሀገሪቷንና ሕዝን በመናቅ በዝምታቸው መግፋትን የወደዱት። ይህ ነገር ከሃይማኖትም ይሁን ከቀለም፣ ከዘርና ከፖለቲካዊ እሳቤዎች አኳያ የሰው ልጅ ተፈጥሮን ባሕርይና የሀገራትንና የመንግሥታትን ተጻራሪ ድርብ አቋሞችን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። “ሰው ለሰው የሚጨነቀው፣ ምን ዓይነት ሰው ሲጎዳ ወይም ምን ዓይነት ሕዝብና የትኛው ሀገር ችግር ላይ ሲወድቅ/ሲወድቁ ይሆን?” በሚል ከፍተኛ ፍልስፍና ውስጥ የሚያስባ ልዩ አጋጣሚ ፈጥሯል። በእውኑ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሕዝብ በበለፀጉ ሀገሮች የአንድ ንጉሥ-ንግሥት ንብረት ከሆነች ውሻ ያንሳሉን? ንግሥት ኤልሣቤጥ የሚወዷት የቤት ድመት ወይም የንጉሥ አብደላ የቤተ መንግሥት ውሻ ቢሞቱ ሲኤንኤንንና ቢቢሲን የመሳሰሉ ላለው የሚያሽቃብጡ ዓለም አቀፍ የዜና ተቋማት የመክፈቻ ዜናቸው እንደሚያደርጓቸው አይጠረጠርም። ወትሮም ብሂሉ “ላለው ይጨመርለታል” ነውና። እንደዚህ ያለው አካሄድ በውነቱ ቅስምን የሚሰብርና ከ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሰለጠነ የሚባል ማኅበረሰብ የሚጠበቅ አልነበረም።

በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ እየተደረገ ያለው ሰቅጣጭ የሕይወት ገጠመኝ በሌሎች ሀገራት ሕዝቦች ላይ ቢደረግ ኖሮ በአሁኑ ወቅት ዓለማችን ከዳር እዳር በተቃወሰች ነበር። በዚህ ዘመን እንደኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የተዋረደ የለም፤ ለዚህ ያበቃንም ይበልጡን በየምንሄድባቸው አካባቢዎች ያሉ መንግሥታት ብቻ ሳይሆኑ እቤታችን ያለው እሾህ፣ እዚያው ኢትዮጵያችን ውስጥ በአራት ከሎ ቤተ መንግሥት የመሸገውና በመላዋ ሀገራችን እንደመዥገር የተጣበቀው ወያኔ ነው። ስለዚህ ዋናው ጠላታችን ቤታችን ውስጥ ሁሉንም ነገር ተቆጣጥሮ ለመከራና እንግልት የዳረገን ወያኔ እንጂ ከዚህ ክፉ አውሬ የጭራቆች ቡድን ቀድሞ በኃላፊነት የሚጠየቅ ሊኖር አይገባም። እርግጥ ነው – በችግራቸው ጊዜ በጥሩ እንግዳ ተቀባይነት ከደረስንላቸው ወገኖች ይህን መሰል ግፍና ስቃይ ማየትና መስማት ዕንቆቅልሽ መሆኑ አይቀርም።

የአንድ ሀገር ዜጎች በተለያዩ ምክንያቶች በፍቅርም ይሁን በጠብ፣ በሥራና ለሥራም ይሁን በስደትና በጦር ምርኮኝነት ከሀገራቸው ወጥተው በሌሎች ግዛቶች የሚገኙበት ሁኔታ በተለይ በዚህ ዘመን በስፋት ይስተዋላል። በዚህን ጊዜ ባሉን ዓለም አቀፍ ሕግጋት መሠረት የዜጎች እንቅስቀሰሴና ዝውውር የዲፕሎማሲን መስመር በጠበቀ ሁኔታ ይከናወናል እንጂ እንዲህ እንደሰሞኑ አንዱ በሌላው ላይ ኢሰብኣዊ ድርጊትን አይፈጽምም። “በዚህን ጊዜ ውስጥ ሀገራችንን ለቃችሁ ውጡ፤ ካልወጣችሁ እንዲህና እንዲህ የመሰለ ችግር ይደርስባችኋል” ተብሎ ማሰጠንቀቂያ ይሰጣል እንጂ ድንገት ከመሬት ተነስቶ የሌሎች ሀገራት ዜጎችን ላልተጠበቀ ኢሰብኣዊ ድርጊት ማጋለጥ ሰብኣዊም ሃይማኖታዊም መደላድል የሌለው ዐይን ያወጣ ወንጀል ነው።

የአሁኑን የኢትዮጵያ መንግሥት ተብዬውን ዓይነት ሳይሆን ሁነኛ የሕዝብ አገልጋይ መንግሥታት ባሉባቸው ሀገራት ውስጥ ብዙ አስገራሚ ግን ተገቢና የሚጠበቅ መንግሥታዊ ፈጥኖ ደራሽነትንና ከአደጋ ታዳጊነትን ማየታችን በጣም የተለመደ ነው። ብዙ አብነቶችን መጥቀስ ቢቻልም የቅርብ ጊዜውን የሻሊትን ጉዳይ ብቻ ማውሳት በቂ ነው።

ሻሊት እሥራኤላዊ ወጣት ወታደር ነበር። ቀደም ሲል በሀገራዊ ግዳጅ ላይ እያለ በፍልስጥኤማውያን ይያዝና ሥውር ቦታ ይታሰራል። በሁለቱ ወገኖች መካከል ብዙ ጊዜ የወሰደ ድርድር ይካሄዳል። የአንድ ዜጋ ጉዳይ መላ እሥራኤላውያንን ማወዛገቡን ይቀጥላል። በመጨረሻም ከአንድ ሺህ በላይ እሥረኛ በአንድ ሻሊት አስፈትተው ፍልስጥኤሞች ይህን ወጣት ወታደር ይለቁታል። ለሀገርና ለሕዝብ ተቆርቋሪ መንግሥት ማለት እንደዚህ ነው። እሥራኤል ሕይወት ያለውን ዜጋዋን ብቻም ሣይሆን ለአንድ በጦርነት ለተሰዋና በጠላት ቁጥጥር ሥር የሚገኝ በድን ዜጋዋ ሕይወት ባላቸው በርካታ ምርኮኞች የምትለውጥ ለዜጎቿ ስሱ የሆነች ሀገር መሆንዋን ከበፊትም የምናውቀው ነው። በዘመናችን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በማድረግ ለዜጎች መብት መከበር ከመታገል አንጻር ሣይሆን በየትም ሥፍራ የሚኖሩ ዜጎች ለሀገር ውርደትና ለአጠቃላዩ የሕዝቡ ኅልውና ማክተም ሌት ከቀን ተግቶ በመሥራት አኳያ ከወያኔ መንግሥት ሌላ በዓለም ሌላ ሀገር ሊኖር እንደማይችል በልበ ሙሉነት መወራረድ ይቻላል። እኛ ላይ እሳት ነው የጣለብን።

“ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ” እንዲሉ እኛ ኢትዮጵያውያን እንደእሥራኤል ያለ ለዜጋው እንስፍስፍ መንግሥት ማግኘቱ ቀርቶብን በዚህን ዓይነት አደጋ የበዛበት ወቅት የዜጎቹ ደኅንነት ካልተጠበ የዲፕሎማሲና የንግድ ግንኙነቶቹን እንደሚያቋርጥ ለማስመሰልም ቢሆን በማስፈራራት ለጨፍጫፊው መንግሥትና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት አቤት የሚል መንግሥት ቢኖረን ምንኛ በታደልን ነበር። ወያኔ ግን ተፈጥሮው እንደነዛው እንደጨፍጫፊዎቹ በመሆኑ እዚህ ግባ የሚባል ውኃ የማያነሣ ሰበብ በመስጠት ዜጎች እየተጨፈጨፉ ባሉበት ሁኔታ ሚዲያዎቹ ሁሉ በአሸሸገዳሜ ዘፈን ተሞልተው በሀገር ሰላም የተለመደ የማደንቆሪያ ልማታዊ ተብዬ ፕሮፓጋንዳውን በስፋት ቀጥሎበት ይታያል። ይህም በጣም ያሳዝናል።

ወያኔ ራሱ ህጋዊ መንግሥት የሆነ ይመስል ከሀገር የሚሰደዱ ዜጎችን ከህግ መስመር ውጪ ነው የወጡትና አያገባኝም በሚል ማደናገሪያ ከመንግሥታዊ ኃላፊነቱ እየሸሸ ነው። በመሠረቱ ቀድሞ መምጣት ያለበት ዜግነት እንጂ ሕግ አይደለም። ሰው የሠራው ሕግ በተፈጥሮ ከተገኝ ሰው መቅደም የለበትም። እንኳንስ ለዜጎቹ ምንም ነገር ካላሟላ ጨቋኝ መንግሥት ይቅርና ሁሉም ነገር ከተመቻቸላቸው ያደጉ ሀገሮችም ሳይቀር ከመንግሥታቸው በመቃረን ጭምር ሰዎች በተለያዬ ምክንያት ከሀገራቸው ይወጣሉ። ለምሳሌ ስኖውደን የተባለው አሜሪካዊ በቅርቡ ከሀገሩ ሸፍቶ በራሽያ ውስጥ ይገኛል። በዚህ ሰው ላይ ማንም አካል ተነስቶ ኢሰብኣዊ ድርጊት ቢፈጽምበት የአሜሪካ መንግሥት ራሱ እንደተዋረደ ይቆጥሩታልና ያ ስኖውደንን የሚያንገላታ አካል የዚህችን ልዕለ ኃያል የሆነች ሀገር ጡንቻ ይቀምሳል እንጂ “ከእኛ ጋር ተጣልቶና አስቀይሞን ስለወጣ እንኳን የእጁን አገኘ!” ከሚል የመሠሪዎች ቂም በቀለኝነት በመነሣት አሜሪካውያኑ እጃቸውን አጣጥፈው አይቀመጡም። ወያኔ ግን ተፈጥሮው በቂምና በበቀል የታጀለ በመሆኑ የሣዑዲን መንግሥት እንዲያውም በባለውለታነት እስካሁን ከሰጣቸው ሰፋፊ እርሻዎች በተጨማሪ ሌላ ትላልቅ መሬቶችን በሽልማት ሳይሰጣቸው አይቀርም። ይህ መንግሥት በሀገር ውስጥም በሰው ግዛትም እየገባ ዜጎቹን የሚጨፈጭፍ በመሆኑ ለዜጎች የሚቆረቆር ተፈጥሮ በጭራሽ የለውም። መባጽዮን ጃተኒን በሰላም በተቀመጠበት ኬንያ ውስጥ ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮቹን አሰማርቶ ያሰገደለ ወያኔ ለዜጎች ይቆረቆራል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ሰሞኑንም የግንቦት ሰባትን ሕዝባዊ ኃይል አመራር ለማስገደል እበላ ባይ ወንጀለኞችን አስርጎ ከፍተኛ የነፍስ ማጥፋት ወንጀል ሙከራ ያደረገ የባለጌዎች መንግሥት ራሱ ገፍቶ ያወጣቸውን ዜጎች ደኅንነት ለማስጠበቅ ከወዳጆቹና ከዓላማው አራማጆች የዐረብ መንግሥታት ጋር ይቀያየማል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው። ለሕዝብና ለሀገር ውርደትና አጠቃላይ የሞራልም ሆነ የማኅበራዊ ዕሤቶች ውድቀት የቆመን አካል ደግ ነገር እንዲያደርግ መጠበቅ የወያኔን ሥረ መሠረትና የተፈጥሮ ባሕርይ በቅጡ አለመገንዘብ ነው። መፍትሔው ግን በያንዳንዳችን እጅ ውስጥ ነው።

እንደግንቦት ሰባት ያለው አማራጭ አንድና አንድ ብቻ ነው። ይሄውም ይህን የዜገች ፀር የሆነ የወንበዴ መንግሥት በሁሉም ሥልቶች ተረባርቦ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ነው። ይህ ሲሆን ነው ዜጎቻችን በሚሄዱበት ቦታ ሁሉ አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱ የሚያስችላቸውን የኔ ነው የሚሉት ሕዝባዊና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ማቆም የሚቻለው። ያኔ ነው ኢትዮጵያ ከተቀበረችበት ተነስታ በዜጎቿ የጋራ ምክክርና ስምምነት በአዲስ ጠንካራ መሠረት ላይ የሚገነባ ሁሉንም እኩል የሚያይ፤ ለሁሉም እኩል መኩሪያ የሚሆን መንግሥት ሊመሠረት የሚችለው። ያኔ ነው የሀገራችንን የሰውና የተፈጥሮ ሀብት ለሀገራችን በማዋል ድህነትንና ስደትን በተባበረ ክንዳችን የምንገታው። ያኔ ነው ሀብታችን በግለሰቦች እየተመዘበረ ለጥቂቶች መንደላቀቂያ መሆኑ የሚቀረውና ለሕዝቡና ለሀገሪቱ ዕድገት የሚውለው። ያኔ ነው በዓለም የተበተነው የተማረ የሰው ኃይላችንና በብዙ ዕውቀትና የሕይወት ልምድ የዳበረው ዜጋችን ወደ ሀገሩ መጥቶ ሀገር ቤት ካለው ኃይል ጋር በመተባበር ኢትዮጵያችንን ከገባችበት አረንቋ የሚያወጣትና ትንሣኤዋም በአዲስ መልክ የሚታወጀው። ለዚህ ሁሉ ተጨባጭ ምኞት እውንነት ደግሞ ሁላችን እጅ ለእጅ ተያይዘን ይህን የበሰበሰና የፈራረሰ ግን በቅርጹ ሲታይ ሕይወት ያለው የሚመስል የወሮበሎች መንግሥት በጋራ ትግል ከነሰንኮፉ ፈንቅለን ልንጥለው ይገባል። ዋናው የችግራችን ሁሉ መባቀያ አዲስ አበባ ላይ ቁጭ ብሎ መንስኤውን ትተን በውጤቶች ላይ ብቻ ማዘኑና መቆዘሙ እንዲሁም ባልተቋረጠ የሀዘን ድባብ ውስጥ ተቀምጦ ማንባቱ ዋጋ የለውም። የኛን ሥራ ወደጎን ትተን ወያኔ በሚፈጥራቸው አፍራሽ ተግባራትና ውጤታቸው ዝንትዓለሙን ማላዘኑ የነሱን ዕድሜ ከማራዘም ውጪ ለኛ የሚተርፍ አወንታዊ ፋይዳ የለውም። ከተባበርን የዚህ መንግሥት ዕድሜ ከሣምንታት አይረዝምም፤ ካልተባበርንና አንዳችን የአንዳችንን ጉድጓድ በመቆፈር ተግባር ከተጠመድን ወያኔ በጀመረው መንገድ ቀጥሎ ሀገራችን በለዬለት ሁኔታ ከዓለም ካርታ እንድትሰረዝ ፈቃደኞች ሆነናል ማለት ነው። ምርጫው የኛው ነው።

በመጨረሻም በሰሞኑ የወገኖቻችን ዕልቂት ምክንያት በቀጥታም ይሁን በተዛዋሪ የወያኔው ግፈኛ አገዛዝ ሰለባ የሆኑ ወገኖቻችንን ነፍስ ይማር እንላለን፤ ለቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ውርደቱና ታሪካዊ አንድምታው አሉታዊ ጥላውን ለሚያሳርፍበት ለመላው ሕዝባችንም መጽናናትን እንመኛለን።
Posted by Addisu Wond.

Advertisements

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: