addisnews

I'm standing for real freedom. I regard freedom of expression as the primary right without which one can not have a proper functioning democracy.

“ወደ ፖለቲካው ተመልሻለሁ” – አቶ ልደቱ አያሌው

lidetu
በምርጫ 97 በፊት ኢትዮጵያዊው ማንዴላ ተብለው እንዳልተሞካሹ ሁሉ ከምርጫ 97 በኋላ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አይንህ ለአፈር ከተባሉት ፖለቲከኞች መካከል አንዱ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የቀድሞው የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው ወደ ፖለቲካው መመለሳቸውን አስታወቁ። “ለትምህርት ከ2 ዓመታት በላይ በውጭ ሃገር በመቆየቴ እንዲሁም ከኢዴፓ ሃያ አምስቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት አንዱ ብሆንም፣ በጠቅላላ ጉባኤ ከሊቀመንበርነት ስለወረድኩ የፓርቲው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ስለማልመራ” ከሚድያው ጠፍቻለሁ ያሉት አቶ ልደቱ ወደ ፖለቲካው መመለሳቸውን ያስታወቁት በአዲስ አበባ ከሚታተመው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው።

“በኢትዮጵያ ውስጥ የኢኮኖሚ እድገቱን መካድ ስህተት ነው፤ እድገቱ ዘላቂነት እንደሌለው አለመገንዘብም ስህተት ነው” የሚሉት አቶ ልደቱ “ሦስተኛ አማራጭ” የተሰኘ የኢዴፓ አቋምን በቃለ ምልላቸው ላይ ገልጸዋል።

በቃለምልልሳቸው ላይ ኢሕአዴግ አመጣሁት ስለሚለው ዕድገት አቶ ልደቱ “”የእድገቱ መጠን መንግስት እንደሚለው ሳይሆን፣ ስምንትና ሰባት ፐርሰንት ይሆኖል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይሄም ቢሆን መጥፎ እድገት አይደለም፤ ጥሩ እድገት ነው፡፡ በእርግጥ በኢትዮጵያ ደረጃ ላለ ድሃ አገር ከስድስት ፐርሰንት በታች የወረደ እድገት፤ ኢኮኖሚው እንደተኛ (ሪሴሽን ውስጥ እንደገባ ነው የሚቆጠረው፡፡ በጣም በከፍተኛ ደረጃ ማደግ ነው የሚጠበቅብን፡፡ የሌሎችም አገራትም ታሪክ ያንን ነው የሚያሳየው፡፡ እንደ አሜሪካና እንደ እንግሊዝ አገር አይነት ትልቅ ኢኮኖሚ ውስጥ ሶስትም አራትም ፐርሰንት ማደግ ከባድ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት ኢኮኖሚ ተይዞ ግን፤ ደብል ዲጂት ማደግ ይቻላል፡፡ መጣ የሚባለው እድገት በህብረተሰቡ ህይወት ውስጥ መታየት አልነበረበትም ወይ? ሊታይም ላይታይም ይችላል፡፡ አንድ ኢኮኖሚ ማደግ ሲጀምር ሁሉንም ህብረተሰብ ይጠቅማል ማለት አይቻልም፡፡ ይሄ በየትም አገር ሆኖ አያውቅም፡፡ እንኳን ዘጠና ሚሊዬን ህዝብ ያለበት አገር ይቅርና፣ 3ሚሊዮን ህዝብ ባለበት አገርም ኢኮኖሚው ማደግ ሲጀምር ሁሉም ህብረተሰብ ተጠቃሚ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ ቀስ በቀስ ነው ተጠቃሚው እየበረከተና እያደገ የሚመጣው፡፡ ስለዚህ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ድህነት ይታያል። ድህነት ብቻ አይደለም በርሃብም የሚሰቃዩ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች መኖራቸው ግን እድገት የለም ወደሚለው ድምዳሜ አይወስደንም፡፡ እድገትም ባለበት አገር ሰው ይራባል፤ ሰው በድህነት ይማቅቃል፡፡ እንኳን በእኛ በጀማሪ አገር ቀርቶ፣ የዳበረ እድገት አላቸው የሚባሉ አገሮችም የሚቸገሩ ሰዎች አሉ፡፡” ብለዋል።

“መንግስት የሚፈጥረው ጫና ለተቃዋሚዎች መዳከም አንድ ምክንያት ነው እንጂ ብቸኛ ምክንያት አይደለም፡፡” ሲሉ በቃለ ምልልሳቸው ላይ የተናገሩት አቶ ልደቱ “አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ እኮ ጠንካራ ነው የሚባለው፤ መንግስት የሚያደርግበትን ተጽዕኖ ተቋቁሞ ማሸነፍ ሲችል ነው፡፡ መንግስት ተጽእኖ የማያደርግ ከሆነማ ሁሉን ነገር የተመቻቸ ከሆነማ ትግልም አያስፈልግም። አገራችን እንደ አሜሪካ ሆናለች ማለት ነው። መንግስት ተፅዕኖ የማያደርግ ከሆነ፣ በጣም የምንመኘው ደረጃ ላይ በቀላሉ ደርሰናል ማለት ነው፡፡ ተዝናንተን በምዕራቡ ዓለም እንደምናየው በምርጫ እየተወዳደርን አሸናፊና ተሸናፊ ልንሆን እንችላለን ማለት ነው፡፡ ግን እዚያ ደረጃ ላይ ለመድረስ ቀርቶ ጨርሶ አልተጠጋንም፡፡ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ ጫና የሚያደርግ መንግስት ነው ያለን፡፡ ይህን ለመለወጥም ነው የፖለቲካ ትግል እያካሄድን ያለነው፡፡ ህዝቡን አስተባብረንና አታግለን፤ የመንግስት ጫና እንዲቆምና ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ እንችላለን፡፡ ይልቅስ ትልቅ እንቅፋት የሆነብን ውስጣዊ ችግር እንዳለብን መገንዘብ አለማቻላችን ነው፡፡ ውስጣዊ ድክመቶችን ለመፈተሸ አለማድረጋችን ነው ካንሠር ሆኖ የሚበላን፡፡ በ1997 ዓ.ም ምርጫ ተቃዋሚዎች ጥምረት እየፈጠሩ የህዝቡን ትኩረት በመሳብ በምርጫ ውጤት አምጥተዋል፡፡ የፓርቲዎችን ብርቱ ፉክክር የሚያካሂዱበት ነፃነት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ለ2007 ዓ.ም ምርጫ ግን ጥምረት የመፍጠር ህዝቡን የማንቀሳቀስና ብርቱ ፉክክር የማካሄድ ሁኔታ ጎልቶ አይታይም፡፡” ብለዋል።

በቀጣይ 2007 በሚደረገው የኢትዮጵያ ምርጫ ላይ “መሰረታዊ ለውጥ ይመጣል ብዬ አላስብም፡፡” የሚሉት አቶ ልደቱ ለዚህም ምክንያታቸው “አንደኛ ነገር ገዢው ፓርቲ ከስህተቱ እየተማረ አይደለም፡፡ አሁንም በየቀኑ የሚነግረን፤ ዲሞክራሲ ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲ ሞልቶ እንደተትረፈረፈና ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ለማድረግ ምንም ችግር እንደሌላቸው ነው፡፡ ይህቺ አገር በልማት ብቻ ሳይሆን በዲሞክራሲም እያደረገች እንደሆነ ነው ኢህአዴግ የሚነግረን። ይሄ ቀልድ ነው፡፡ በተጨባጭ ያለው ሁኔታ ኢህአዴግ እንደሚለው አይደለም፡፡ የዲሞክራሲ ስርዓት በአግባቡ በዚች አገር እንዲያብብ እያደረገ አይደለም። ገዢው ፓርቲ ላይ ቁርጠኝነት እየታየ አይደለም፡፡ በተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩልም አብዛኛው ውስጣዊ ድክመታቸውን ሳይፈትሹ ነባሩን አስተሳሰብና አቀራረብ እንደያዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ በ2007 ዓ.ም ምርጫ፣ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ መሠረታዊ ለውጥ ቢመጣ የሚችለው እነዚህ ሁለት ጐራዎች ከስህተታቸውና ከችግራቸው ተምረው የተግባር ማሻሻያዎችን ሲያደርጉ ነው። ይሄን ሲያደርጉ አይታይም፡፡ አሁን የቀረው አንድ ዓመት ነው፡፡ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ መንገዳቸውን ካላስተካከሉ፣ ምርጫው ከአለፉት ምርጫዎች የተሻለ ይሆናል ብዬ አላምንም፡፡” የሚል ነው።

ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ኦፍ ለንደን ፤ ስኩል ኦፍ ኦሬንታል ኤንድ አፍሪካን ስቴዲስ የሚባል ውስጥ “ዲቨሎፕመንት ስተዲስ አጥንቼ ወደ ሃገሬ ገብቼ መኖር ጀምሬያለሁ ሲሉ ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ የተናገሩት አቶ ልደቱ “ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ ኢዴፓ ‹‹ሶስተኛ አማራጭ›› የሚል ሃሳብ ይዟል፡፡ ይሄ ሃሳባችሁ ከምን አደረሳችሁ?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ “ሶስተኛ አማራጭ ሲባል፣ ልዩ የርዕዮተ አለም መስመርን ለመግለጽ ሳይሆን፣ የአቀራረብና የስልት ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፓለቲካ፣ እስከ አሁን ድረስ ሁለት ፅንፍ የያዘ ነው። ሁለትም ነገር መደገፍ ወይም ሁሉንም ነገር መቃወም፡፡ የገዥው ፓርቲ አባል ከተሆነ፤ ተቃዋሚ የሚሰራውን ነገር ሙሉ በሙሉ ማጥላላት፤ የተቃዋሚ አባል ከተሆነ ደግሞ መንግስት የሚሠራውን ነገር ሁሉ መቃወም፡፡ እንዲህ ሁለት ጫፍ የያዘ አሰላለፍ፤ ለአገራችን ፖለቲካ አልጠቀመም፡፡ ከመቻቻል ከመደማመጥ አርቆናል፡፡ ለዚህም ነው፤ ከሁለቱ ጽንፎች የተለየ አማራጭና የተለያየ አቀራረብ ያስፈልጋል የሚል አስተሳሰብ ይዘን የመጣነው፡፡ በመንግስትም ሆነ በተቃዋሚ የተሠራ ነገር ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም ከሆነ ልንደግፈው ይገባል፡፡ የማይጠቅምና የሚጐዳ ከሆነ ደግሞ በተጨባጭ መረጃ መቃወምና እንዲቀየር መታገል ያስፈልጋል፡፡ በስሜታዊ ጽንፍ ሳይሆን በምክንያታዊ አስተሳሰብ ነው ፖለቲካው ሊመራ የሚገባው፡፡ አለበለዚያ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወደ ዲሞክራሲያዊ የመቻቻል ባህል ሊቀየር አይችልም። ሁለት ስሜታዊ ፅንፎችን ይዞ፣ ብሔራዊ መግባባት ለማምጣት በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ፣ ምክንያታዊ አስተሳሰብ ነው የሚያዋጣን ብለን ሶስተኛ አማራጭ ይዘናል፡፡ ይሄንን አቀራረብ ይዘን ስንመጣ ፈተናዎች ገጥመውናል፡፡ ሁለቱ ጽንፎች ለረዥም ጊዜ ስር የሰደዱና የከረሩ ስለነበሩ፣ ብዙ ሰዎች የእኛን አስተሳሰብ ለመቀበል በጣም አስቸግራቸዋል፡፡ ደግሞም አያስገርምም፡፡ ሰዎች በቀላሉ ይሄን አስተሳሰብ የሚቀበሉ ከሆነ፤ ከመነሻው የአገራችን ፖለቲካ ከባድ ችግር የለበትም ማለት ነው፡፡ የአገራችን ፖለቲካ ግን ለረዥም ጊዜ የዘለቀ ትልቅ ችግር አለበት፡፡ ስለሆነም፤ ሦስተኛ አማራጭ ብለን ያቀረብነው የምክንያታዊ አስተሳሰብ አቅጣጫችንን ብዙ ሰዎች በቀላሉ ሊቀበሉት አልቻሉም። “ተቃዋሚ ከሆንክ በቃ ማንኛውንም ነገር ትቃወማለህ፡፡ ኢህአዴግም ከሆንክ ማንኛውንም ነገር ትደግፋለህ፤ ሌላ ሦስተኛ አማራጭ የለም” የሚል የተዛባ አመለካከት ይሰነዘርብን ነበር፡፡ “እንዲያውም ሦስተኛው አማራጭ የምትሉት ነገር ወላዋይነት ነው” በማለት ውዥንብር የመፍጠር ነገርም ነበር። በሂደት ግን፣ ብዙ ሰው ጉዳዩን እያብላላው፣ እያጤነውና እየተገነዘበው እንደሆነ አይተናል፡፡ እኛ በምንፈልገው ፍጥነት ህብረተሰቡ ተረድቶታል የሚል እምነት የለንም፡፡ ገና ብዙ ይቀራል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እስከአሁን በመጣበት የጽንፈኝነት መንገድ የትም ሊያደርሰን እንደማይችል ብዙዎች እየገባቸው ነው፡፡ ሁለቱ ጽንፎች የሚፈጥሩት ቅራኔና ውጥረት፣ ከዴሞክራሲ እያራቀን እንጂ ወደ መቻቻል እያመጣን እንዳልሆነ ሰው እየተገነዘበው ነው፡፡
“ሁለቱ የፅንፍ ሃይሎችና ጐራዎች አይጠቅሙም ትክክል አይደሉም” የሚለው አስተሳሰብ እየጐላ መጥቷል፡፡ “ሁለቱም ፅንፎች አይጠቅሙም፤ ችግር አለባቸው” ከተባለ ክፍተት መኖሩን ነው የሚያሳየው፡፡ ያንን ክፍተት የመሙላት ጉዳይ ነው የሶስተኛው አማራጭ ፋይዳ፡፡ ይሄንን አስተሳሰብ ይዘን እንደነበር በተለይ በፓርላማ በነበረን ተሳትፎ በደንብ ማሳየት ችለን ነበር፡፡ ፓርላማ ውስጥ ሌሎች ተቃዋሚዎች ከሚያራምዱት አስተሳሰብ በተለየ ሁኔታ፣ መንግስት ከሚሠራቸው ነገሮችና ከሚያራምዳቸው አቋሞች ውስጥ ለህዝብና ለሀገር የሚጠቅም ነገር ስናገኛቸው በድፍረት ስንደግፍ ታይቷል፡፡ ሰው ለዛ የሚሠጠው ትርጉም ምንም ይሁን እኛ ለሀገርና ለህዝብ ይጠቅማል ብለን እስካመንበት ድረስ በድፍረት ወጥተን፤ ይሄ አቋም ከገዢው ፓርቲም ይምጣ ከተቃዋሚ ፓርቲም ይምጣ ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም እስከሆነ ድረስ እንደግፋለን ብለን ማሳየት ችለናል፡፡ ገዢው ፓርቲ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮችን ሲሰራ ደግሞ ከሌሎች ተቃዋሚዎች በበለጠ በመረጃ በተደገፈ ከመተቸትና በጠነከረ መልኩ በመታገል ምክንያታዊነታችንን ማሳየት ችለናል፡፡ ከተቃዋሚ ፓርቲ ውስጥም ጥፋት ወይም ድክመት ሲኖር፣ ተቃዋሚ ነውና እሱን አንነካውም አንልም፡፡ እንዲስተካከል እንተቻለን፡፡ ለሰላማዊ ትግልና ለአገር የማይበጅ፣ ለመቻቻል ፖለቲካ ማይጠቅም ሆኖ ካገኘነው፣ ተቃዋሚውንም ቢሆን በድፍረት የመተቸት አዲስ ባህል ይዘን መጥተን አሳይተናል፡፡ ያን የማይወዱ ሰዎች ብዙ ነበሩ፡፡
“በሂደት እየተረዱ ሲመጡ፣ ግን እኛ የያዝነው አቋም ትክክል እንደሆነ መገንዘብ የቻሉ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ ይሄ አቋማችን በአገራችን ያልተለመደ አዲስ አቋምና አካሄድ ስለሆነ፤ አንዳንድ ሰዎች በእኛ ላይ የሚያወሩትን አሉባልታ ማራገብ ተጠቅመውበታል። በእኛ ላይ ከንቱ ጥርጣሬና ጥላቻ እንዲስፋፋ በማድረግ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፈዋል። በሌላ በኩል ግን ከነባሩ የጽንፈኝነት ፖለቲካ የተለየ ምክንያታዊ ፖለቲካ ማራመድ ለዚህ አገር እንደሚያስፈልግ በደንብ ለማሳየት ችለናል፡፡ ስለዚህ ሦስተኛ አማራጭ ይዘን መምጣታችን፣ ጥቅምም ጉዳትም ነበረው፡፡ ከአጭር ጊዜ አንፃር፣ ሊያስወድድ የሚችል የፖለቲካ አቋም አልነበረም፡፡ ለአሉባልታ አጋልጦናል፡፡ ከረጅም ጊዜ አንፃር ግን ይሄ ምክንያታዊ የፖለቲካ መስመራችን እየሰፋና እያደገ፣ በተለይ በአዲሱ ትውልድ ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ የሚመጣ አቋም ነው፡፡ ስለዚህ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የበለጠ እየተጠናከረ ነው፡፡ ግን ሂደቱን እኛ ስለተናገርነውና ስላራመድነው ብቻ ውጤት ያመጣል ማለት አይደል፡፡ ከአጠቃላይ ከአገራቱ ሶሽዬ ኢኮኖሚክ የእድገት ደረጃ ጋር ተያይዞ ነው ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችለው፡፡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ወጥቶ ስለተናገረ ብቻ፣ የበቃ የፖለቲካ አመለካከት ያለው ህብረተሰብ ይፈጠራል ማለት አይደለም፡፡ እንደዛ አይነት ህብረተሰብ የሚመጣው ኢኮኖሚያችን ሲያድግና ሲዳብር፤ ትምህርት ሲስፋፋና ከሌላው አለም ጋር መስተጋብራችን የበለጠ ሲጠናከር ነው፡፡ በአጭር ጊዜ የሚቀየር ነገር አይደለም፡፡ የአስተሳሰብ ለውጥ እውን የሚሆንበት ሂደት በጣም የተራዘመ እንዳይሆንና እንዲፋጠን በማድረግ ረገድ ግን የኢዴፓ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡” ሲሉ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በአቶ ልደቱ ወደ ፖለቲካው መመለስ ዙሪያ የዘ-ሐበሻ ተከታዮች ምን ትላላችሁ?
Posted by Addisu Wond.
http://www.zehabesha.com/

Advertisements

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: