addisnews

I'm standing for real freedom. I regard freedom of expression as the primary right without which one can not have a proper functioning democracy.

ቆይታ ከጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ እና ከአቶ በቀለ ገርባ ጋር

12
ሰሞኑ ጥቂት ጋዜጠኞች ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት አምርተን ነበር። ወደ ማረሚያ ቤቱ የሄድነው ወዳጃችን ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬን ለመጠየቅ ነበር።
ጋዜጠኛ ውብሽት ከኩላሊት ህመም ጋር በተያያዘ ከዝዋይ ማረሚያ ቤት ወደ ቃሊቲ መዛወሩን በመስማታችን ነበር ለጥየቃ ወደ ቃሊቲ ያመራነው።
ከቀኑ አምስት አካባቢ ይሆናል። አስፈላጊውን ፍተሻ አጠናቀን ወደ ውስጥ የዘለቅነው። ቀኑ የአዘቦት ቀን በመሆኑ በማረሚያ ቤቱ የጠያቂዎች መጨናነቅ
አልነበረም። ፍተሻውም ሆነ ሥነስርዓቱ ሰላማዊ ነበር። ታራሚዎችና ጠያቂዎች ወደሚገናኙበት ቦታ ስንደርስ ማንን ለመጠየቅ እንደመጣን ተናግረን ውብሸትን
መጠባበቅ መርን። ሲቪል ከለበሱ የማረሚያ ቤቱ አስተባባሪዎች አንዱ የድምፅ መነጋገሪያ (ማይክ) አንስቶ ከፍ ባለ ድምፅ ደጋግሞ የውብሸትን ስም ጠራ።
ብዙም ሳይቆይ ውብሸት መጣ። በዚህ አጋጣሚ የማረሚያ ቤቱ አስተባባሪዎች ያሳዩን ትብብር በመልካምነቱ ሊጠቀስ የሚገባው ነው። ትብብራቸውና ቀናነታቸው
የተለየ ስለነበር ሊመሰገኑ ይገባል። ውብሸት በርከት ያልን የሙያ አጋሮቹን ሲመለከት ፊቱ ላይ የመደነቅ ስሜት ይታይ ነበር። ፈጠን ባለ እርምጃ ሣቅ ባሞቀው
ገፅታ እኛ ወዳለንበት አካባቢ መጣ። በእንጨት በታጠረው ፍርግርጉ ላይ እየተንጠራራን ሰላምታ ተለዋወጥንና ወጋችንን ቀጠልን። የወጋችን መጀመሪያ የጤንነቱ ጉዳይ
ነበር። እንደተባለውም ካለፉት አራት ወራት ወዲህ የኩላሊት ህመም ላይ መሆኑን ነገረን። “ከእኔ የባሱ አልጋ ላይ የወደቁ ታራሚዎች እያሉ የእኔን ጉዳይ ማስጮህ አልፈለኩም።
ነገር ግን ሕመሙ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ በመምጣቱ ሕክምና እንዳገኝ ጥያቄ አቀረብኩ” ብሎናል። “በተፈጥሮዬ መድሐኒት መውሰድ አልወድም” የሚለው ጋዜጠኛ ውብሸት ህመሙ ቢበረታም ታመምኩ ብዬ ጥያቄ ማቅረቡን አልፈለኩትም። ነገር ግን ከውሃ ሽንቱ ጋር ደም እየተቀላቀለ መውጣቱ በኩላሊቱ ላይ ከበድ ያለ ችግር ማጋጠሙን በመረዳቱ ለህክምና ጥያቄ ለማቅረብ መገደዱን ይገልፃል። ባቀረበው የህክምና ጥያቄ መሠረት በመጀመሪያ አልትራሳውንድ መነሳቱን፣ በኋላም ውጤቱ በመጥፋቱ በድጋሚ መነሳቱንና
ውጤቱም በኩላሊቱ ውስጥ አሸዋ የሚመስል ነገር የሚያሳይ መሆኑን ገልጾልናል። ውጤቱ ይሄን ቢመስልም የማረሚያ ቤቷ ዶክተር “ውሃ ጠጣበት” ከማለት ባለፈ ህክምና አለማግኘቱን ገልጿል። ወትሮውንም “በተፈጥሮዬ በርከት ያለ ውሃ እጠጣለሁ” የሚለው ጋዜጠኛ ውብሸት “ውሃ ጠጣበት” የሚለው የሕክምና ምክር ባለፈ ተጨማሪ ሕክምና እንደሚያስፈልገው ተናግሯል። በዝዋይ ማረሚያ ቤት የታንከር ውሃ በመጠጥነት መጠቀሙ ምናልባትም ለኩላሊት ህመሙ መንስኤ ሊሆን እንደሚችል የሚጠቅሰው ውብሸት፤ ለዚሁ ችግር ትኩረት እንዲሰጥ በዚሁ አጋጣሚ ገልጿል። “ሕክምና እንዳላገኝ የተደረገው ሆን ተብሎ ነው ብዬ መቀበል ይቸግረኛል” ያለን ጋዜጠኛ ውብሸት ታራሚዎች ተገቢውን ህክምና የማግኘት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተያዙ ሰዎች መብት ከመሆን ባለፈ የሰብአዊነት ጉዳይ መሆኑን አስታውሷል። በሽብርተኝነትም ሆነ በሌላ በማናቸውም መልክ የተከሰሱ ፍርደኞች
ሚዛናዊና ፍትሐዊ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ተገቢ መሆኑንም ጠቅሷል። የማረሚያ ቤት ህይወት በርካታ አስቸጋሪ መልኮች እንዳሉት ፍርደኞችም ቢሆኑ መብታቸው መከበር እንዳለበት ጋዜጠኛ ውብሸት ሳይናገር አላለፈም። በአሁኑ ወቅት ያለበት ማረሚያ ቤት ውስጥ ከሁለት መቶ በላይ ታራሚዎች ጋር መታሰር አስቸጋሪ መሆኑንም ነግሮናል። ከአእምሮ መታወክ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ፍርደኞች ጉዳይ በሌሎች ፍርደኞች ላይ ጉዳት የሚያደርሱበት አጋጣሚ በመኖሩንና ለዚሁ ችግርም መፍትሄ መፈለጉ ተገቢም ተመካሪም እንደሆነ ገልጿል። ጋዜጠኛ ውብሸት ይሄንን ሁሉ ነገር ያጫወተን ቡና እየጋበዘን ነበር። ውብሸት ማረሚያ ቤት ሆኖ “ብሉ ጠጡ” ያለን እቤቱ ብንሄድ ምን ሊሆን እንደሚችል ታሰቦኝ ነበር። በዕለቱ ልንጠይቀው የሄድነውን ሁሉ እንደየምርጫችን ቡና፣ ማኪያቶና ለስላሳ ጋብዞናል። ግብዣው ፍቅር የተሞላበትና ደጋግመን እንድንጠይቀው የሚያደርግ ነበር።
ውብሸትን እያነጋገርንበት በነበረበት ወቅት አንድ አዛውንት መጥተው ሰላም አሉን። አዛውንቱ በተመሳሳይ በሽብርተኝነት ክስ ጥፋተኛ ተብለው የ13 ዓመት ፍርደኛ ናቸው።
ወዲያው ደግሞ አንድ ጎልማሳ ፍርደኛ መጥቶ ሰላምታ ሰጠን። ይህም ሰው የተመሳሳይ ክስ ፍርደኛ ነው። ይህንን ፍርደኛ ከሌሎች የሚለየው ሜዲካል ዶክተር መሆኑ ነው።
ጋዜጠኛ ወዳጃችንን ለመጠየቅ ሄደን “እነእገሌ ደህና ናቸው” የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። “እነእገሌ” ከተባሉት መካከል አቶ በቀለ ገርባ አንዱ ነበሩ። በአጋጣሚ እኚህ
ምሁር ፍርደኛ ፍርዳቸውን እየፈፀሙ ያሉት ከእነ ውብሸት ጋር ስለነበር ተጠርተውልን መጡ። አቶ በቀለ ገርባ 26 ዓመት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ልሳን መምህር እንደነበሩ
ቢነግሩንም የሰውነት አቋማቸው ግን ገና 26 ዓመታትን የሚሰሩ ያስመስላቸዋል። ቁምጣ በነጠላ ጫማ ተጫምተዋል። ዘና ባለ መንፈስ ሰላምታ ተለዋወጥን። አቶ በቀለ ስክነትና
መረጋጋት በፊታቸው ላይ ይንፀባረቃል። ሲናገሩ በስሜት ሳይሆን በረጋ መንፈስ ነበር። በሽብርተኝነት ክስ ጥፋተኛ መሆናቸውበፍርድ ቤት በመረጋገጡ 3 ዓመት ከ8 ወር
ነበር የተፈረደባቸው። በመጀመሪያ ስምንት ዓመት ቢፈረድባቸውም ተከራክረው ወደ 3 ዓመት ከስምንት ወር ዝቅ በማስደረጋቸው የአመክሮ ጊዜአቸው ተቃርቧል። ይህንን መብት
የሚያገኙ ከሆነ በመጪው ጥር እሳቸውና ቃሊቲ ሊለያዩ ይችላሉ። አቶ በቀለ በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ወቅት ያሳዩት መልካም ባህሪ የአመክሮ መብታቸውን እንደማያሳጣቸው ተስፋ አድርገዋል። “የሆነው ሁሉ የምጠብቀው ነበር” የሚሉት አቶ በቀለ፤ በዚህም ወቅት በሀሰት ጥሩ ያልሆነ አጋጣሚ በስተቀር የሚረብሻቸው ነገር እንደሌለ ነበር
የጠቀሱት። የሁለት ወጣት ልጆች አባት የሆኑት አቶ በቀለ በተመሳሳይ ክስ ጥፋተኛ ሆኖ የዕድሜ ልክ ፍርደኛ ለሆነው አንዱዓለም አራጌ የነበራቸውን አድናቆት “የተለየ” ወይም
(Unique) በሚል ቃል ነበር የገለፁት። ለአንድ ዓመት አብረው በታሰሩበት ወቅትና የመድረክ የስራ አስፈፃሚ አባል ሆነው በሰሩባቸው ጊዜአት ይበልጥ መተዋወቃቸውን ይናገራሉ። አቶ በቀለ በታሰሩበት ወቅት ባለቤታቸውም ከስራ በመባረራቸው ለጥቂት ጊዜያት በቤተሰባቸው ላይ መጉላላት ቢያጋጥምም አሁን ግን ባለቤታቸው የግል ስራ በመስራት ኑሮን ለማሸነፍ እየተጣጣሩ መሆኑንም፣ ልጆቻቸውም ቢሆኑ አንዳንድ ለጋሽ ሰዎች እየረዱአቸው እየተማሩ መሆኑን በመጥቀስ ፈጣሪያቸውን አመስግነዋል። የማረሚያ ቤት ህይወት አስቸጋሪ መልኮችን በሰፊው ያወጉን አቶ በቀለ በታራሚዎች መካከል እኩልነት ሊኖር እንደሚገባም መስክረዋል። በማረሚያ ቤት አቅርቦት ከቃሊቲ ይልቅ ዝዋይ በተነፃፃሪ ሻል
ያለ መሆኑንም ሳይጠቅሱ አላለፉም።አቶ በቀለም ሆኑ ጋዜጠኛ ውብሸት የሀገሪቱ የፖለቲካ ልዩነት መቻቻልና በመግባባት መንፈስ እንዲቃኝ ያላቸውን በጎ ስሜት ገልፀዋል። በተለይ ጋዜጠኛ ውብሸት በሙያው ተስፋ አለመቁረጡን ነው የገለፀው። “ከዚህ ማረሚያ ቤት ብወጣ ጁስ ቤት አልከፍትም፤ ተመልሼ ጋዜጠኛ ነው የምሆነው” በማለት ለሙያው ያለውን ታማኝነት ገልጿል። የመቻቻልና የእርቅ መንፈስ ለሀገር እንደሚበጅ የሚሰብከው ውብሸት፤ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በደቡብ ሱዳን ተገኝተው ሁለቱን ወንድማማቾች ለማስታረቅ የሄዱበትን ርቀት በእኛም ሀገር ቢተገብሩት እንዴት መልካም ነበር ሲል ምኞቱን ገልጿል።

Source-http://ethioforum.org/
Posted by Addisu Wond.

Advertisements

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: