addisnews

I'm standing for real freedom. I regard freedom of expression as the primary right without which one can not have a proper functioning democracy.

የአቦይ ስብሐት ከኢትዮጵያዊነት መውደቅ

(ፋክት መጽሄት)
‹‹ከኢትዮጵያዊነት መውደቅ ማለት ምን ማለት ነው? አፄ ሀይለስላሴ ከኢትዮጵያዊነት ወድቀዋል የሚል የለም፡፡ ኮሎኔል መንግስቱንም የሚል የለም፡፡ . . . ከኢትዮጵያዊነት መውደቅ ማለት፤ በቃ በአጭሩ ኢትዮጵያዊ አለመሆን ነው፡፡ ሌላ ማንነት መገንባት (IDENTITY DEVELOP) ማድረግ ነው፡፡›› ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፣ ኢትዮ-ምህዳር፣ ቅጽ 02፣ ቁጥር 47፡፡

ሀሳብን በመግለፅ ነፃነት እጅግ አድርጌ አምናለሁ፡፡ እንዲያውም ብዙዎች ‹የዲሞክራሲ መገለጫው ነፃ-ምርጫ ነው›፣ የሚሉትን ወረድ አድርጌ፣ ‹ዋናው የዲሞክራሲ መገለጫ ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት ነው›፣ ብዬ አምናለሁ፡፡ ነፃና ዲሞክራሲያዊ የሚባለው ምርጫ በምስጢር የሚከናወን መሆኑ ነፃ ያለመሆኑ ማስረጃ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት ግን እንደ ነፃ ምርጫ በምስጢር የሚደረግ አይደለም፡፡ በዚህ ተራ ምክንያት ነው ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት፣ ከነፃ-ምርጫ የላቀ ዲሞክራሲያዊ ስርአትን ገላጭ ሆኖ የሚሰማኝ፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ሀገሬን ሳያት ‹ነፃ› ምርጫን ያህል፣ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት አልተሳካላትም፡፡ ለዚህ ነው ተቃማዊ ፓርቲ መስርተው በ‹ነፃ› ምርጫው ለመሳተፍ ከሚጥሩት የበለጠ፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ ነፃነትን ለማበረታታት ለሚውተረተሩት ልቤ የሚደነግጠው፡፡ ለአቦይ ስብሀትም የተለየ ግምት ያደረብኝ በዚሁ የተነሳ ይመስለኛል፡፡ ፓርቲያቸው በተደጋጋሚ በ‹ነጻ› ምርጫ ቢያሸንፍም፣ የዲሞክራሲ መገለጫው ነፃ ምርጫ ነው ብለው አልተቀመጡም፤ ለሃሳብ ነፃነት መረጋገጥ ከፍተኛ ማበረታታት እያደረጉ ነው፡፡ በእድሜዬ፣ በደርግም ሆነ በኢህአዴግ፣ ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል እንደ እሳቸው የሀገራችንን ሁለንተናዊ ሁኔታ አስመልክቶ በነፃነት (ሀሳቡን በሾመው መንግስት ሀሳብ ሳይቃኝ) የሚገልፅ አላጋጠመኝም፡፡ በዚህ የተነሳ ለአቦይ ስብሀት ትልቅ አድናቆት አለኝ፡፡
ለዚህ ጽሁፌ መነሻ የሆነኝም የአቦይ ስብሀት ህዳር 17፣ 2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ተማሪዎች ጋር ያደረጉት ውይይት ነው፡፡ እንደ ብዙዎቹ አወዛጋቢ የአቦይ ስብሀት አስተያየቶች፣ በዚህ ውይይት ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች የሰጡዋቸውን አስተያየቶች አንብቤና ግራ ተጋብቼ ብቻ ላልፋቸው አልፈለኩም፡፡ ጥያቄ አዘል አስተያየቴን ልሰነዝር ወደድኩ፡፡
መቼም ለረዥም አመታት ታግሎና አታግሎ፣ በታላቅ መስዋእትነት በተገኘ ድል፣ የተገኘ ስልጣን ይዞ፣ ሀገርና ህዝብ የሚመራ ሰው በጋዜጣና በመጽሔት፣ በሬዲዮና ቲቪ፣ በስብሰባና በአውደጥናት የሚጽፈውና የሚናገረው፣ ‹ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት አለ፤ ሀሳቤን ለመግለጽ አልፈራም› ለማለት ሳይሆን፣ የሚያስተላልፈው ቁምነገር ስለሚኖር ነው፡፡ ለመሆኑ የአቦይ ስብሀት የዩኒቨርሲቲው ንግግር፣ ወደፊት ሀገር ለሚረከቡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚጠቅም፣ ምን ጠብ የሚል ቁም ነገር (ከእሳቸው የህይወት ልምድና የፖለቲካ ሰውነት አንፃር) አለው?፡፡
እንደ እኔ እምነት ማንም ባለስልጣን እንደሳቸው ቁምነገር ሲናገር ሰምቼ አላውቅም፡፡ አንዱን እውነት ጠቅሼ ልሟገት፡፡ ‹‹ከኢትዮጵያ ህዝብ በላይ የኤርትራ ህዝብ ኢትዮጵያዊነት አለው፡፡›› ብለዋል አቦይ ስብሀት፡፡ ብዙዎች ይህን ሲሰሙ ወይም እንደኔ ተጽፎ ሲያነቡ፣ ውሸት ብለው ደንግጠው አዝነዋል፡፡ እኔ ግን እውነት ተናግረዋል እላለሁ፡፡ በእሳቸው (ምናልባም ደርግን ባስወገዱልን አብዛኞቹ ነፃ አውጪዎቻችን) አመለካከት የእኛ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያዊነት ከኤርትራውያን ያነሰ ነው፡፡ በመሆኑም ጠንካራ ኢትዮጵያዊነት አላቸው የተባሉት ኤርትራውያን፣ ያነሰ ኢትዮጵያዊ ናችሁ ከተባልነው የበለጠ ኢትጵያዊ መብት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ዘመንና አጋጣሚ የመረቃቸው ኤርትራውያን በሀገራቸው ጥሩ ኤርትራዊ፣ በሀገራችንም ጥሩ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ እኛ እዚህ ኢትዮጵያዊ እዚያም ኤርትራዊ አይደለንም፡፡ ከኤርትራ ንብረታችን ተዘርፎ ስንባረር፣ የኤርትራ መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጵያም መሪዎች ውሸት ብለው አላግጠውብናል፡፡ ለምን? እዚያ በኤርትራዊነት ስለሚበልጡን መሪዎቹ ዘርፈው አባረሩን፡፡ እዚህ በኢትዮጵያዊነት ስለሚበልጡን መሪዎቻችን አፊዘው ተቀበሉን፡፡ እውነቱን ብለዋል አቦይ ስብሀት! በመሪዎቻችን ሚዛን ኤርትራውያን በኢትዮጵያዊነት ይበልጡናል፡፡ ምን ኤርትራውያን ብቻ! ‹‹ለኤርትራ ብቻ ሳይሆን ለሶማሊያ፣ ለሱዳን፣ ለጅቡቲም፣ ለኤርትራም አትራፊ መሆን የእኛ የቤት ስራ ይመስላል፡፡›› ያሉት አቦይ ስብሀት ጅቡቲ፣ ሱዳንና ሱማሌስ በኢትዮጵያዊነት ስለሚበልጡን አይደል! እንግዲያማ በኮረንቲ በቀን አስሬ መጥፋት እቃችን እየተቃጠለ፣ ቋት የገባ እህል ሳይፈጭ እያደረ፣ በየቢሮው ያለስራ እየተዋለ፣ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሱዳን ድረስ፣ የኮረንቲ መስመር ዘርግተው ለምረቃ ይሄዱ ነበር!
በቀደም በሳዑዲ አረቢያ በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን መከራና ግድያ በሰላማዊ ሰልፍ እንዳንቃወም የተደረገው በመሪዎቻችን ሚዛን ኢትዮጵያዊነታችን ቀሎ በመገኘቱ ይመስለኛል፡፡ አቦይ ስብሀት እንዳሉት ከእኛ የበለጠ ኢትዮጵያዊነት ያላቸው ኤርትራውያን አዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ቢጠይቁ ይፈቀድላቸው የነበረ ይመስለኛል፡፡
xxx
Posted by Addisu Wond.

Advertisements

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: