addisnews

I'm standing for real freedom. I regard freedom of expression as the primary right without which one can not have a proper functioning democracy.

ዛሬ የሚያስፈሯሯችሁን እስከ ዘላለሙ የማትሰሙበት ግዜ ይመጣልና አትፍሩ

1111111111111
ህወሃት የሚያራምደው የዘረኝነት ፖለቲካና፤ የተዘፈቀበት የሙስና አዘቀት ሊወጣ ከማይችልበት አዙሪት ውስት ከተውታል።ከእንግዲህ ወዲህ ለህወሃቶች የቀራቸው አንድ አማራጭ ብቻ ነው። ሁሉንም ዜጎች በዘረኝነት ሰንሰለት አስሮ ቀጥቅጦ እና አፍኖ መግዛት ቀጣዩ ቅዥታቸው ነው።

የዚህ አፍኖ የመግዛት ቅዥታቸው መገለጫም ዜጎች ህወሃት ስለሚፈፅመው ወንጀል ምንም ዓይነት መረጃ እንዳያገኙ ማድረግ አንዱ ነው።ህወሃት የሚፈፅመው ወንጀል ከህዝብ ዓይንና ጆሮ ተሠውሮ እንዲረሳ ይመኛል። ይሄን ምኞቱን እውን ለማድረግም ሌሎች ነፃ ሚዲያዎችን አሸባሪ ማለት ወይም ደግሞ ሌላ የተሰወረ አጀንዳ ያላቸው እያለ ማላዘንን ሥራየ ብሎ ተያይዘውታል። ከሰሞኑ አዲስ አበባ ውስጥ የሚታተሙ ስምንት የግል ህትመቶችን አሸባሪዎች በማለት ክስ መስርተዋል። አስቀድመው ፈርደው ከጨረሱ በኋላ ክስ መመሥረት የህወሃቶች የተለመደ የፍትህ ሥርዓት ነው። በአገሪቷ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ግዜ ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ ሁኖ የተቋቋመውን ኢሳትንም አሸባሪ እያሉ ሰሚ አልባ ጩኸት እየጮኹ ነው። የኢሳት ቴሌቭዥንና ሬዲዮንን የሚሰማም በአሸባሪነት ይከሰሳል እያሉ በየዜጎች ደጅ እየተንከላወሱ ለማስፈራራት እየሞከሩ ነው።

እኛ ግን እንዲህ እንላለን !!! አትፍሩ ! አትፍሩ ! አትፍሩ ! ኢሳትን ሰምታችኋል ብሎ የሚያስፈራሯችሁን ለዘላለሙ የማትሰሟቸው ግዜ እየመጣ ነው። የነፃነት ጎህ ቀዶ ሁላችን የፈለግነውን ሰምተን፤ ያልፈለግነውንም የምንተውበት ዘመን እሩቅ አይደለም። ግንቦት ሰባት የፍትህ የነፃነት እና የእኩልነት ንቅናቄም የተቋቋመው ዜጎች ያለማንም ጣልቃ ገብነት የወደዱትን ወስደው፤ የጠሉትን መተው የሚችሉበትን መንገድ ለማመቻቸት ነው። ዘረኞቹ በደምና አጥንት ታውረው ጭካኔን ከጀግንነት ቀላቅለው እኛ ብቻ ወንድ ባሉበት መንደር ሌላ ጀግና ኢትዮጵያዊ ወንድ ገስግሶ የሚመጣበት ዕለት እየደረሰ ነውና እንዳትፈሩ እንመክራችኋለን። ህወሃቶች ዜጎችን ከሰው በታች አድርገው ለመግዛት እንዲመኙ ያደረጋቸው እብሪት የሚተነፍስበት ዘመን እሩቅ አይሆንምና አሁንም አትፍሩ።

ህወሃቶች ከእነርሱ ቁጥጥር ውጪ ያሉ ነፃ ሚዲያዎችን እንደማይታገሱ የታወቀ ነው። ለምን ቢሉ የወንጀላቸው ብዛት፤ የክፋታቸው ጥልቀት ሳይነገር ተሠውሮ እንዲቀር ስለሚመኙ ነው። ይህን ምኞታቸውን እውን ለማድረግም ራሳቸው የሠረቱን ህግ ውልቅልቁን አውጥተው ያፈራርሱታል። ዜጎች መረጃ የማግኘት መብት አላቸው ተብሎ እነርሱ “ህገ-መንግስታችን” እያሉ በሚጠሩት ላይ በማያሻማ ሁኔታ የተቀመጠ ቢሆንም እነርሱ ግን ለራሳቸው ህግ መታመንን አልመረጡም። እንዲያውም እነርሱ ሞተንለታል የሚሉትን ህግ አፈር አስገብተው ራሳቸው ህግ ሆነው ተፈጥረዋል። እነርሱ ህግ ሁነው በመፈጠራቸውም በየዜጎች ደጅ እየተንከላወሱ ኢሳትን ብትሰሙ ወዮላችሁ እያሉ ያስፈራራሉ። ዜጎች ግን የሞኝ ዘፈናቸውን መልሰው መልሰው ለሚያላዝኑ ኢሕአዴጋዊያን ዛቻ የሚንበረከኩ አይሆኑም። አገራቸውን በተመለከተ ማንኛውንም መረጃ ለመስማት ያላቸውን ነፃነትም ለምናምንቴዎች አሳልፈው የሚሰጡ አይሆኑም።

ጎሬቤታችን ኬኒያ ከአስር በላይ የግል ቴሌቭዥን ጣቢያዎች አሏት።በርካታ በአጭር ሞገድና በኤፊኤም ሞገዶች የሚተላለፉ ሬዲዮኖችም አሏት። የኬኒያ መንግስት ለዜጎቹ ክብርና ፍቅር ስላለው የተቻለውን ያክል ነፃ ሚዲያ እንዲኖር ይጥራል። ለህዝቡ ክብርና ፍቅር የሌለው ህወሃት ግን በወረቀት ላይ በፃፈው ህግ ዜጎች መረጃ የማግኘት መብታቸው ያልተገደበ ነው ቢልም በተግባር ግን የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት ያፍናል። ነፃ ሚዲያ እንዳይፈጠር ለማድረግ፤ የተፈጠሩትንም ለማጥፋት ግዜውንና የአገሪቷን ሃብት በከንቱ ያባክናል። ህወሃት ከድሃ ጉሮሮ እየነጠቀ ኢሳትን ለማፈን በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር አባክኗል። የአገሪቷ የህግ ተቋማትም ሌቦችንና ነፍሰ ገዳዮችን መከታተል ትተው በነፃነት እንፃፍ ብለው የተነሱ ጋዜጠኞችን በማሳደድ የአገሪቷን የሥራ ሠዓትና ሃብት በከንቱ ያባክናሉ። ህወሃቶች ይሄው ናቸው። አገር፤ ወገን፤ ህዝብ የሚባል ነገር በሂሊናቸው ያልተፈጠረ፤ እነርሱ ብቻቸውን ሌላውን ተጭነው መኖር የሚፈልጉ፤ የጨካኞችና የእብሪተኞች ስብስብ መሆኑን መዘንጋት አያስፈልግም።

የተከበራችሁ ያገራችን ዜጎች !

አገራችሁን በተመለከተ መረጃ ማግኘት የዜግነት መብታችሁ መሆኑን እንዳትረሱ። ይሄም እነርሱ “ህገ-መንግስት” ብለው በሚጠሩት ላይም በግልፅ ተቀምጧል። ይሄን በህግ ደንግጎ ሲያበቃ ኢሳትንና ሌሎችን ነፃ ሚዲያዎችን መስማት አትችሉም ሲል የማውቅላችሁ እኔ ነኝና የምትሰሙትንና የምታዩትን የምመርጥላችሁ እኔ ነኝ እያለ መሆኑን አስታወሱ። ይሄ ማለት አዋቂው እኔ እንጂ እናንተማ ክፉን ከደጉ ለመለየት ገና አልደረሳችሁም ማለት መሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል።መንግስት ነኝ ብሎ በአገሪቷ ጫንቃ ላይ የተቀመጠው ህወሃት-ኢሕአዴግ ህዝቡን የማያከብር ብቻ ሳይሆን ለህዝብ ያለው ንቀትም ወሰን የሌለው ሁኗል። ይሄ ዘረኛና ዘራፊ ቡድን ክብራችንን አዋርዶና አንገታችንን አስደፍቶ ሊገዛን አይገባውም። ፍርሃት ይብቃ። ህወሃት እየፈጠረ ያለው ፍራቻን መሸሸ አይገባም፤ ይሄን ፍርሃት መጋፈጥ የጀግና ተግባር ነውና ለክብራችሁና ለነፃነታችሁ ስትሉ ፍርሃቱን ተጋፈጡት እንጂ አትሽሹት።

በዚያ በጨካኞች መንደር ሁናችሁ በሠላማዊ ትግል ብቻ ለውጥ እናመጣለን ብላችሁ የተደራጃችሁ የፖለቲካ ድርጅቶችም መረጃ የማግኘት፤ መረጃ የመሰብሰብ እና የማሰራጨት መብታችሁ ነው ብለን ልንነግራችሁ አንዳዳም። በነፃ ሚዲያ መናገርም ሆነ ለማንኛውም ሚዲያ መረጃ የመስጠት ማንም የሚሰጣችሁ መብት እንዳልሆነ ታውቃላችሁ። እኛ እንደምንገምተው ኢሳትም ሆነ ሌሎች ነፃ ሚዲያዎች የእናንተም ሃብት ናቸው። ህወሃት-ኢሕአዴግ አትስሙ ወይም ደግሞ አትናገሩ ሲላችሁ ያንን የእብሪተኛ ትዕዛዝ አለመቀበላችሁን ለነፃ ሚዲያዎች መረጃ በመስጠትና ሃሳባችሁን በነፃው ሚዲያ በመግለፅ እምቢተኝነታችሁን በማሳየት ለምትመሩት ህዝብ አርአያ እንድትሆኑ ብናሳስባችሁ ደፈሩን እንደማትሉ ተስፋ እናደርጋለን። ከዚህ አንፃር ሰማያዊ ፓሪትና አንድነት ያወጡትን መግለጫ በአድናቆት የምንመለከተው መሆኑን ለማስታወቅ እንወደላን።

ለህወሃት-ኢሕአዴጎች !

ራሳችሁን ከአሸባሪ ምግባርና መዝገብ ማስፋቅ ሳትችሉ የነፃነት ፍላጎት ያላቸውን ሁሉ አሸባሪ እያላችሁ ማላዘናችሁን የምታቆሙበት ግዜ እየመጣላችሁ ነው። እናንተ ከላይ ሁናችሁ ህዝቡ ከሥር ሁኖ እናንተን ተሸክሞ ለዘላለም እንደማይኖር አበክረን ልናሳውቃችሁ እንወዳለን።በየሰው ደጅ ካድሬዎቻችሁን ልካችሁ ኢሳትን አትስሙ እያላችሁ የማስፈራራት እብሪታችሁ ረገብ የሚልበት ግዜ እየመጣላችሁ ነው። ዛሬ ህዝባችንን የእኛን ብቻ ስሙ፤ የእነርሱን አትስሙ ማለታችሁ ለህዝባችን ያላችሁን ንቀት የሚያመላክት ነው።ህዝባችንን እንደናቃችሁና እንዳዋረዳችሁ አትቀጥሉም። የነፃነትን ፍላጎት አፍናችሁ አታቆሙትም። የፍትህ ጥማታችንን በአፈሙዝ ልትገቱት አትችሉም። የእኩልነትን ጥያቄ በውሸትና በዛቻ አታዳፍኑትም። እውነት እውነት እንላችኋለን ወንጀላችሁ ሳይነገር፤ በስውር የዘረፋችሁት በአደባባይ ሳይገለጥ አይቀርም። እኛም ቀንና ማታ ለዚያ ግብ ሳናገራግር እየሰራን ነው። በአገራችን የነፃነት ጎህ ሳይቀድ ለሽፋሽፎቶቻችን እንቅልፍ፤ ለስጋችንም ዕርፍት አይሆንም። የዘረኞችና የዘራፊዎች ጀንበር ሳትጠልቅ፤ የእኩልነት ናፋቂዎች ጎህ ሳትቀድ አናርፍም። ያነገታችሁት መሣሪያ የሸንበቆ ምርኩዝ እስከ ሚሆን የጀመርነውን ትግል ዕለት ዕለት እያጎለበትነው እንቀጥላለን።

ህወሃት-ኢሕአዴጎች ሆይ ስሙ! ይሄን ህዝብ ከሚችለዉ በላይ ገፍታችኋታል። ህዝቡም ሊሸከማችሁ ከሚገባ በላይ ተሸክሟችኋል።እንዲህ ህዝባችንን መፈናፈኛ አሳጥታችሁ እና እስከ ልጅ ልጆቻችሁ ረግጣችሁ ለመግዛት ያለማችሁት ህልም በህልምነቱ ብቻ እንደሚቀር ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ አይግባችሁ። ትግላችን ጥሩ መሠረት ይዟል። ከዚህ በኋላ ወደ ኋላ የሚመልሰን ምድራዊ ኃይል የለም።እውነት እውነት እንላችኋለን ለዘላለም ኢትዮጵያዊያንን አዋርዳችሁ የመግዛት ህልማችሁ ቅዥት መሆኑን ደግመን ልንነግራችሁ እንወዳለን።

በህወሃት-ኢሕአዴግ ውስጥ ሁናችሁ የነፃነት፤ የፍትህ እና የእኩልነት ጥያቄያችንን የምትጋሩን ወገኖቻችን እሰክ አሁን የምታደርጉት የውስጥ ትግል ፍሬ እያፈራ ነው። ፍሬውን በራሪ ወፍ እንዳይለቅመው የተለመደው ጥንቃቄ እንዳይለያችሁ ይሁን። አሁን ህዝቡ መረጃ እንዳያገኝና፤ መረጃ እንዳይሰጥ የሚሞከረው ሙከራ ህገ-መንግስት ተብየውን የሚጥስ መሆኑን ታውቃላችሁ። ይሄን ካድሬው ሁሉ እንዲገነዘበው የውስጥ ትግሉ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ራሱ ያወጣውን ህገ መንግስት አፈራርሶ ከትቢያ የሚቀላቅል ቡድን በምን ሞራል ብቃት ነው ሌላውን ህገ-መንግስቱን ሊንዱ ነበር እያለ የሚከሰው ? በኢትዮጵያዊያን ላይ የተጫነው ህገ-መንግስት በህወቶች ሲፈርስ ትክክል ፤በሌላው በተግባር እንዲውል ሲጠየቅ ደግሞ ስህተት ሁኖ በአሸባሪነት የሚያስከሥሥ መሆኑን ግንዛቤ መጨበጥ ይጠቅማል።

በመጨረሻም በህወሃት-ኢሕአዴግ የጭቆና ቀንበር ሥር ለምትንገላቱ ወገኖቻችን ሆይ ! አትፍሩ። ይህን የሚያስፈራራችሁን አካል እስከ መጨረሻው የማትሰሙበት ዘመን እየመጣ ነው። አሁን ፍርሃታችሁን ግደሉት።የምትሰሙትንና የምታዩትን እኔ ነኝ የምመርጥላችሁ ከሚል እብረተኛ እጅ ራሳችሁን ለማላቀቅ የግንቦት ሰባት ንቅናቄ እያደረገ ያለውን የነፃነት፤ የፍትህና የእኩልነት ትግል ተቀላቀሉ።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

Advertisements

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: