addisnews

I'm standing for real freedom. I regard freedom of expression as the primary right without which one can not have a proper functioning democracy.

ጎንደር በሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄዎች ተወጥራለች

በዘሪሁን ሙሉጌታ

በመጪው እሁድ ጥር 25 ቀን 2006 ዓ.ም በጎንደር ከተማ ሰማያዊ ፓርቲ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር መካከለል ጉዳይ ለሕዝብ ግልፅ አለመሆኑን በመቃወም ሰልፍ የጠራ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ቀን በጎንደር ዙሪያ የሚኖሩ የቅማንት ብሔረሰብ አባላት ማንነታችን አልተከበረም በሚል ሕገ-መንግስታዊ ጥያቄአቸውን ለማቅረብ የሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄ አቅርበዋል።
ለጎንደር ከተማ አስተዳደር ሁለቱም ወገኖች የሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄ ቢያቀርቡም፤ ለሁለቱም ወገኖች ለሰላማዊ ሰልፉ መካሄድ ማረጋገጫ አለማግኘታቸውን እየተናገሩ ነው። ሰማያዊ ፓርቲ ሰልፉን ለማስተባበር ወደስፍራው የላከውን የፓርቲውን አመራር ጨምሮ ሌሎች የፓርቲው አስተባባሪዎች ታስረው መፈታታቸውን ገልጿል። ሆኖም ሰልፉን ለማካሄድና የማሳወቂያ ደብዳቤ ለከተማው አስተዳደር ቢያቀርቡም አስተዳደሩ ደብዳቤውን ባለመቀበሉ ጠረጴዛ ላይ ትተው መውጣታቸውን የፓርቲው ሕዝብ ግንኙነት አስታውቋል። እስካሁን የከተማው አስተዳደር ምንም አይነት ምላሽ ያልሰጠ በመሆኑ ሰላማዊ ሰልፉ እንደተፈቀደ በመቁጠር ሰልፉን ለማካሄድ በዛሬው ዕለት 12 የአመራር አባላት ያሉት ቡድን ወደ ጎንደር እንደሚሄድ አስታውቋል።
በሌላ በኩል በበርካታ ጊዜያት የቅማንት ብሔረሰብ የቋንቋ፣ የባህልና የማንነት መብቱ አልተጠበቀም የሚሉ ወገኖች በተመሳሳይ ቀን (ጥር 25 ቀን 2006 ዓ.ም) ጥያቄአቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ለመጠየቅ ሰልፍ መጥራታቸውን የቅማንት ብሔረሰብ የማንነት የራስ አስተዳደር ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ አበራ አለማየሁ ለሰንደቅ ጋዜጣ አስታውቀዋል።
የኮሚቴው ሊቀመንበር የጎንደር ከተማ በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር ጥረት ማድረጋቸውን ገልፀዋል። አስተዳደሩም የእነሱ ጥያቄ ሕገ-መንግስታዊ እንጂ የፖለቲካ አይደለም። ነገር ግን እናንተ ጥያቄ ካቀረባችሁ በኋላ ሰማያዊ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ ጠይቋል በማለት አጀንዳችሁ ተመሳሳይ ነው የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው አጀንዳችን የተለያየ መሆኑን ብንገልጽም፤ “በጥይት ትመታላችሁ፣ መትረየስ ጠምደን እንፈጃችኋለን” እያሉ እያስፈራሩን ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ጥር 4 ቀን 2006 ዓ.ም በጅልጋ ወረዳ አይከል ከተማ ላይ ከ70 ሺህ በላይ ሕዝብ የተገኘበት ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸውን ያስታወሱት አቶ አበራ፤ በዚያን ጊዜም “በመትረየስ እንፈጃችኋለን” ቢሉንም ሕዝቡ ነቅሎ መውጣቱን ተናግረዋል። አሁንም በጎንደር ከተማ ከሰማያዊ ፓርቲ ቀድመው ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ቢዘጋጁም በየቀበሌው ሕዝቡን በስብሰባ በመጥራት ወደ ሰልፉ እንዳይወጡ ቅስቀሳ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም ያለውን ጫና ተቀቁመው ሰልፉን ለማካሄድ ወደኋላ እንደማይመለሱ ተናግረዋል።
እንደ አቶ አበራ ገለፃ፤ እነሱ የሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄ ተቀባይነት ያላገኘው በተመሳሳይ ቀን ሰማያዊ ፓርቲ በሌላ አጀንዳ ሰልፍ በመጥራቱ እኛም ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር አብረን እንደምንሰራ ተደርጎ ታይቶብናል ብለዋል። ይሁን እንጂ የእኛ ጥያቄ ሕገ-መንግስታዊ እንጂ የፖለቲካ ወይም የድንበር አይደለም ብለዋል።
የቅማንት ብሔረሰብ በአማራ ክልል በጎንደር የተለያዩ ወረዳዎች የሚኖር ሕዝብ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አበራ፤ የሕዝብ ብዛቱም አንድ ሚሊዮን እንደሚሆን፣ የቋንቋው ተናጋሪዎችም ከ20 ሺህ በላይ እንደሚሆኑ ገልፀው፤ ሕዝቡ እራሱን በቻለ ዞን ለመተዳደር ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል ብለዋል። በያዝነው ዓመት መስከረም ወር ጥያቄውን ለፌዴሬሽን ም/ቤት አቅርቦ ውሳኔ አለማግኘቱንም ተናግረዋል። የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ጌትነት አማረን በስልክ አግኝተን በዚሁ ጉዳይ ላይ የአስተዳደራቸውን አቋም እንዲያብራሩልን ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።

መንግስት የህትመት ውጤቶች አከፋፋዮች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ፍንጭ ሰጠ

በዘሪሁን ሙሉጌታ

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል በሀገሪቱ ውስጥ ፈርጀ ብዙ ኀሳቦች ለህብረተሰቡ እንዳይደርስ እያደረጉ ነው ባሉዋቸው የጋዜጣና መፅሔት አከፋፋዮች ላይ መንግስት በፍጥነት የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቁ።
ሚኒስትር ዴኤታው ይሄህን የተናገሩት “የዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግስትና የመገናኛ ብዙኃን ግንኙነት” በሚል ርዕስ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጆርናሊዝምና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት በኢንተርኮንቲነታል ሆቴል ሰሞኑን ባዘጋጀው የአንድ ቀን ሲምፖዚየም መዝጊያ ላይ ነው። የፕሬስ ነፃነት አፈና ሲነሳ በአከፋፋዮች አማካኝነት የሚደረግ አፈና አንዱ መሆኑን በመጥቀስ ጥቂት መፅሔቶችንና ጋዜጦችን በባለቤትነት የያዙ ግለሰቦች የማከፋፈል ስራውን በሞኖፖል ይዘው የአመለካከት ፈርጀ ብዙነት እንዳይኖር በማድረግ፣ በርካታ ህትመቶችን በለጋነታቸው ለሞት እንዲበቁ በማድረግ የአፈና ስራ ውስጥ የገቡ ወገኖች አሰራራቸው በፍጥነት መስተካከል አለበት ብለዋል።
“ሚዲያን የመደጎምና የማስተካከሉ ስራ መንግስት በአግባቡ በተጠና ሁኔታ መግባት እንዳለበት ያምናል” ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው በሚዲያ የኀሳብ ገበያ ውስጥ ምቹ ሁኔታዎችን በማዘጋጀት ለኢንዱስትሪው ቀና እድገት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል። በአከፋፋዮች በኩል በርካታ ችግሮች ተለይተው እየተጠኑ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የህትመት ሚዲያው ብቻ ሳይሆን የሕዝብ የመገናኛ ብዙኀን አውታሮች ከችግሮች ነፃ አለመውጣታቸውንም የጠቀሱት አቶ ሽመልስ መንግስት ፈጣን መረጃ የሚሰጥ የሚዲያ ስርዓት እንዲፈጠር እንደሚፈልግ ገልጸዋል። መንግስት መረጃዎችን በገፍ የሚያቀርብ፣ ጥራት ባለውና ወቅታዊ በሆነ መንገድ የሚሰራ የሚዲያ ስርዓት እንዲገነባ ይፈልጋልም ብለዋል።
ብሔራዊ የሚዲያ ፖሊሲው በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ የህብረተሰቡን የፖለቲካ ብዙሃነት፣ ባህላዊና ሀይማኖታዊ ፈርጀብዙነት ከመቀበል የሚነሳ መሆኑ አስታውሰው፤ ነገር ግን ሚዲያው በማንኛውም የባለቤትነት ውስጥ ቢሆንም ብሔራዊ መግባባትን ለማስረፅ መተኪያ የሌለው ቀዳሚ ሚና እንዲጫወት ፍላጎት እንዳለው ገልፀዋል። ሚዲያው በብሔራ ዊ መግባባት ላይ እንዲሰራ መንግስት ቢፈልግም ከማንኛውም ርዕዮተዓለም ተፅዕኖ ነፃ እንዲሆን ይፈልጋል ብለዋል።
አሁን ያለው የሚዲያ ችግር በንግድ ሚዲያ መርህ ወይም በገበያ መርህ መንቀሳቀስ አለመቻል መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሽመልስ አብዛኛዎቹ ሚዲያዎቻቸው ገበያቸውን ከማስታወቂያ የሚሸፍኑ አይደሉም ብለዋል።
“በአብዛኛዎቹ የህትመት ሚዲያዎች ላይ የሚታየው ማስታወቂያ “እንጥል እቆርጣለሁ፣ ግግ እቧጥጣለሁ” የሚል የአንድ ደብተራ ማስታወቂያ ነው። ከዚህ ውጪ ሌላ ማስታወቂያ የላቸውም። ኮሜርሺያል አይደሉም፤ ኮሜሪሻያል ካልሆኑ ይደጎማሉ። በድጎማ የሚተዳደሩ ከሆነ ታማኝ አንባቢ ነው ያላቸው። ከተወሰኑ ርዕዮተአለማዊ አጥሮች አልፈው መጓዝ አይፈልጉም። ስለሆነም የህትመት ሚዲያ እድገት ላይ አንድ ትልቅ ጋሬጣ የሆነው ከነፃ ሚዲያ ህግጋት ውጪ ተንጋዶ የበቀለ የሚዲያ አካሄድ ነው” ያሉት አቶ ሽመልስ ይህንን ለማስተካከል መንግስትን ጨምሮ ሁሉም ወገኖች ሊተባበሩ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ አዘጋጆች ከተመሰረተባቸው ክስ ነፃ ወጡ

በአሸናፊ ደምሴ

ተፈፅሟል ያሉትን የመልካም አስተዳደር ግድፈት አስመልክቶ በኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ላይ ባወጡት ዘገባ ምክንያት በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ የ300 ሺህ ብር የፍትሃብሔር ክስ የተመሰረተባቸው የጋዜጣዋ አዘጋጆች በትናንትናው እለት ሐዋሳ በሚገኘው የሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበው ከተመሰረተባቸው ክስ ነፃ ወጡ።
የሁለቱን ወገኖች ክርክር ሲያደምጥ የቆየው የሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በትናንትናው ዕለት ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት፤ ተከሳሾች በተከሰሱበት ጉዳይ ላይ ማስተካከያ በማድረጋቸው፤ የዩኒቨርስቲው የስራ ባልደረቦች በፈፀሙት የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በከሳሽ በኩል ያልተካደና እውነተኛ ነገር መሆኑን አስረድቷል።
በሌላም በኩል ከሚዲያ ተቋማት ግብ አንፃር ብልሹ አሰራሮች አሉ ማለታቸው በህግ የተሰጣቸው ሃላፊነት በመሆኑ እና እውነት የሆነን ክስተት ለመዘገብ ፈቃድ የማያስጠይቅ መሆኑን በማስታወስ የዩኒቨርስቲውን አርማ (Logo) መጠቀምም ከህግ አንጻር ተቋሙ የንግድ ተቋም ሳይሆን የህዝብ ተቋም ነው ሲል ተከሳሾችን የሚያስጠይቃቸው ነገር የለም ብለን በማመናችን በነፃ አሰናብተናል ብሏል።
በመሆኑም ከሳሹ የሐዋሳ ዩኒቨርስቲ በፍትሃብሄር ካቀረባቸው መከራከሪያ ሀሳቦች መካከል አንደኛው የጋዜጣው አዘጋጅ ችሎቱ ዩኒቨርስቲና አርማ ሳያስፈቅድ ተጠቅመዋል የሚል ሲሆን ለዚህም ፍርድ ቤቱ ተቋሙ የንግድ ሳይሆን የህዝብ ተቋም ነው ሲል ውድቅ ያደረገው ሲሆን፤ ሁለተኛው መከራከሪያቸው የነበረው ደግሞ በዩኒቨርስቲው ውስጥ ብልሹ አሰራር አለ በማለት ባወጡት ዘገባ የተቋሙ ስም እንዲጠፋ አድርገዋል የሚል ሲሆን ለዚህም የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰጠው ውሳኔ፤ ዘገባው እውነት በሆነ ነገር ላይ ተመስርቶ የተሰራ በመሆኑ ከሚዲያ አላማ አንጻር ትክክል ነው ሲል ውድቅ አድርጎታል። በከሳሽ በኩል ሌላኛው መከራከሪያ ሆኖ የተጠቀሰው በዘገባው ውስጥ ስማቸው የተጠቀሱት ግለሰቦች የቡድን መሪዎች እንጂ የዩኒቨርስቲው አስተዳደር አባላት አይደሉም የሚል ሲሆን፤ ለዚህም ተከሳሾቹ ከዩኒቨርስቲው ያገኟትን በማህተምና በፊርማ የተረጋገጠ የሹመት ደብዳቤ ለፍርድ ቤት አቅርበው ያስረዱ በመሆኑ የዩኒቨርስቲውን ክስ ውድቅ ማድረጉን ገልጿል።
ይህም በመሆኑ የግራ ቀኙን ክርር ሲያደምጥ የሰነበተው የሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በትናንትናው እለት የኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ አዘጋጆችን በነፃ ማስገባቱን በውሳኔ ንባቡ አስታውቋል። ይህን ውሳኔ መሰረት አድርጎ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝም የሁለቱም ወገኖች የይግባኝ መብት የተጠበቀ መሆኑን፤ ተከሳሾች የውጪና ኪሳራ ዝርዝር የማቅረብ መብት ያላቸው መሆኑንና መዝገቡ በውሳኔ ወደመዝገብ ቤት መመለሱን አትቷል።
የከፍተኛ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ አስመልክቶ የጋዜጣዋ ዋና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደተናገረው ፍርድ በማግኘታችን ደስተኞች ነን ያለ ሲሆን ነገር ግን በዚህ ሁሉ ወጣ ውረድ ውስጥ በቀዳሚነት የስራ ባልደረባዬንና የጓደኛችን ጤና አጥተናል፤ ከስድስት ጊዜ በላይ ከአዲስ አበባ ሐዋሳ በመመላለሳችን ለበርካታ ውጪና እንግልት ተጋልጠናል፤ በስራችን ላይም ከፍተኛ ጫና አሳድሮብናል ሲል በሀዘኔታ ተናግሯል። በመሆኑም ከጠበቃቸው ጋር ተመካክረው ሊያገኙ የሚገባቸውን ወጪና ኪሳራ አስልተው ጥያቄያቸውን እንደሚያቀርቡም ጠቁሟል።

እስክንድር ነጋ
ለ2014 ጎልደን ፔን ፍሪደም ሽልማት ተመረጠ

በዘሪሁን ሙሉጌታ

በኢትዮጵያ የፕሬስ እንቅስቃሴ በአሳታሚነት፣ በጋዜጠኝነትና በብሎገር (ድረገጽ ጋዜጠኝነት) የሚታወቀው በአሁኑ ወቅት በሽብርተኝነት ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ የ18 ዓመት ፍርድ የተፈረደበት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የ2014 ዓ.ም ጎልደን ፔን ፍሪደም ዓመታዊ ሽልማት አሸናፊ ሆነ።
ላለፉት ሦስት ዓመታት በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በእሥር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ለሽልማቱ የበቃው መንግስትን የሚተች ጽሁፍ በመፃፉ መሆኑን ተቋሙ አስታውቋል።
ተቋሙ የዓለም የጋዜጦች ማኅበር (World Association of News Papers) እና የአሳታሚዎች ማኅበር (News Publishers) ሲሆን ከጋዜጠኝነት እና ከአሳታሚዎች ማኅበር ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግዙፍ ተቋም ነው።
ተቋሙ ሽልማቱን ለጋዜጠኛ አስክንድር ከመስጠቱ በፊት ለኢትዮጵያ መንግስት ማሳሰቢያ መላኩን፣ በማሳሰቢያውም ላይ የፀረ-ሽብር ሕገ-መንግስትን በሚተቹ ጋዜጠኞች ለእስር የሚዳርግ በሽብርተኝነት፣ በሚዲያና በሕግ ላይ የሚያተኩረውን የቬይና ዴክላሬሽንን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን የሚቃረን መሆኑን ማስረዳቱን ጠቅሷል።
የኢትዮጵያ መንግስት እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሌሎች ጋዜጠኞችን ማለትም የሙስሊሞች ጉዳይ መፅሔት ሪፖርተር ሰለሞን ከበደ፣ ውብሸት ታዬ፣ ርዕዮት አለሙ እና የሱፍ ጌታቸው ከእስር እንዲለቀቁ መጠየቁን የዓለም አቀፉ የጋዜጦችና አሳታሚዎች ማኅበር ፕሬዝደንት ቶማስ በርንጋርድ አስታውቀዋል።
“ሽልማቱ ለጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የተበረከተው በሀገሩ አፋኝ እና ተለጥጦ እየተተረጎመ ባለው የፀረ-ሽብር ሕግ መኖሩን እያወቀ ባሳየው ብርታት ነው” ሲሉ የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ጨምረው ተናግረዋል።
በጋዜጠኞችና በአሳታሚዎች ማኅበራት ስር ለሙያው አስተዋፅኦ ላደረጉ ጋዜጠኞች በየዓመቱ የሚበረከተው የጎልደን ፔን ኦፍ ፍሪደም ጠቀም ያለ የገንዘብ ሽልማት እንደሚኖረው ይታወቃል። ተቋሙ እ.ኤ.አ ከ1961 ጀምሮ ከሙያው ጋር በተያያዘ አስተዋፅኦ ላላቸው ወገኖች ሽልማት ሲሰጥ ቆይቷል። ተቋሙ ከግለሰቦች ባለፈ ለፕሬስ ነፃነት ከፍተኛ መስዋዕትነት ለሚከፍሉ ቡድኖችም ሆነ ተቋማት ዓመታዊ ሽልማት ይሰጣል። የዘንድሮው የተቋሙ ተሸላሚ የሆነው ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋም በመጪው ሰኔ ዘጠኝ ቀን 2014 ጣሊያን ቶሪኖ ከተማ የዓለም ጋዜጠኞች ኮንግረንስ፣ የኤዲተሮች ፎረም፣ የዓለም የማስታወቂያ ፎረም እና የዓለም የፕሬስ ጉባኤ ዝግጅት ላይ እንደሚበረከትም ለማወቅ ተችሏል።
የዓለም ጋዜጦችና አሳታሚዎች ማኅበር ለትርፍ ያልተቋቋመ፣ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም ሲሆን፤ በውስጡም 76 ብሔራዊ ጋዜጦች ማኅበራት፣ 12 የዜና ወኪሎች፣ 10 ክፍለ አህጉሪዊ የፕሬስ ድርጅቶች እንዲሁም በመቶ ሀገራት የሚገኙ ጋዜጦች አባላትን የያዘ ግዙፍ ተቋም ነው። ተቋሙ እ.ኤ.አ በ1948 የተመሠረተ ሲሆን፤ እስከ 2011 ባለው ጊዜም በጠቅላላ በዓለም ላይ 18 ሺህ አሳታሚዎችን የሚወክል ማኅበር ነው።
ይህ ማኅበር ለፕሬስ ነፃነት እውን መሆን የሚሰራ ሲሆን፤ ለጋዜጣ ሕትመት እድገትና ዓለም አቀፍ ትብብር የሚሰራ ተቋም ነው። በተጨማሪም የዩኔስኮ፣ የተባበሩት መንግስታት እና የአውሮፓ ካውንስልን የሚያማክር ትልቅ ተቋም ነው።

የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ የወጪ ንግድ ዝቅተኛ አፈጻጸም ተመዘገበ

በፍሬው አበበ

በ2006 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የሆልቲካልቸር ምርቶች የወጪ ንግድ አፈጻጸም ደካማ እንደነበርና በተለይ የፍራፍሬ ምርቶች ኤክስፖርት እጅግ አነስተኛ አፈጻጸም መታየቱ ተመለከተ።
የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው ከሐምሌ 1 ቀን 2005 እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2006 ዓ.ም የሚኒስቴሩን ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ትላንት ሲያቀርቡ እንዳሉት ከሆልቲካልቸር ምርቶች ማለትም አበባ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ 202 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ እንደነበር አስታውሰው የተገኘው ግን 106 ሚሊየን ዶላር ብቻ ነው። ይህ የእቅዱን 53 በመቶ መሆኑን አስረድተዋል። ከመጠን አንጻር ሲያብራሩም አበባ 70 በመቶ፣ አትክልት 77 በመቶ፣ ፍራፍሬ 34 በመቶ ማከናወን መቻሉን አቶ ተፈራ አስታውቀዋል። ዘርፉ አነስተኛ አፈጻጸም ሊያስመዘግብ የቻለው ለአዲስ አልሚዎች የሚሆን መሬት በሚፈለገው ፍጥነትና መጠን ማዘጋጀት አለመቻል እና ሎጀስቲክ መሰረተ ልማት በተዘረጋላቸው የክልል ክላስተሮች ለዘርፉ ልማት ተጨማሪ መሬት ለይቶና ተገቢ መሰረተ ልማት በሟሟላት ነጻ አድርጎ የማዘጋጀት ስራ በፍጥነት ማጠናቀቅ አለመቻል ናቸው። እነዚህን ማነቆዎች በመፍታት ውጤታማ የሆኑ አዳዲስ ባለሃብቶች በመመልመል ማስገባት እንዲሁም የዘርፉን ማነቆዎች በመፍታት ረገድ የአምራችና ኤክፖርተሮች ማህበርን በማሳተፍ ለመስራት መታሰቡ ተመልክቷል።
አቶ ተፈራ ከም/ቤቱ አባላት ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በሆልቲካልቸር ዘርፍ አነስተኛ አፈጻጸም ሊመዘገብ የቻለው በዋንኛነት በዘርፉ አዳዲስ ባለሃብቶች እና ሰፋፊ መሬት ወደስራ ማስገባት ካለመቻሉ ጋር በቀጥታ የተያያዘ እንደነበር አስታውሰው ችግሩ ከክልሎችም ጋር በመነጋገር በመፈታት ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

በቡራዩ ከተማ በመሬት ሽያጭ ስም 270 ሺህ ብር ያጭበረበረው ግለሰብ ጥፋተኛ ተባለ

በአሸናፊ ደምሴ

በተለያዩ ጊዜያት በቡራዩ ከተማ የሚገኝን 140 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው መሬት በማሳየትና በማሳሳት አስራ ሶስት ከሚደርሱ ሰዎች 270ሺህ ብር በማታለል የማይገባውን ጥቅም አግኝቷል ሲል ዐቃቤ ሕግ ክስ የመሰረተበት ተከሳሽ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 16ኛ ወንጀል ችሎት በትናንትናው ዕለት ጥፋተኛ ተባለ።
የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው፤ ተከሳሽ አቶ ፍቃዱ ዋጋሪ የማይገባውን ብልፅግና ለማግኘት አስቦ 2002 ዓ.ም በተለያዩ ጊዜያት በልደታ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 05/08 ክልል ውስጥ የግል ተበዳዮችን በተናጠል በማግኘት ቡራዩ ከተማ ውስጥ በህጋዊ መንገድ የተቀበልኩት 140 ካሬ ሜትር ቦታ አለኝ በማለት የራሱ ያልሆነን ቦታ በማሳየትና አሳሳች ነገሮችን በመናገር እንዳግባባቸው የሚያትት ሲሆን፤ በተጨማሪም በተለያዩ ጊዜያት በልደታ ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኘው መስቀል ሆቴል በመቅጠር በቁጥር 125668 የተመዘገበና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የቡራዩ ከተማ ልማት ቢሮ የሚል ብር 7720 የተከፈለበት ሀሰተኛ ደረሰኝ ለግል ተበዳዮች በመስጠት ለጠቅላላ የቦታው ዋጋ 30ሺህ ብር ከእያንዳንዳቸው በመውሰዱ በፈፀመው የማታለል ወንጀል ክስ መስርቶበት ነበር።
ተከሳሽ በአራት ተበዳዮች ብቻ አራት ክሶች የተመሰረቱበት ይሁን እንጂ በአጠቃይ በግለሰቡ ማጭበርበር የተበደሉት ሰዎች ቁጥር 13 ሲሆኑ ጠቅላላ ያወጡት ወጪም 270 ሺህ እንደሚደርስ ታውቋል። ይህም ሆኖ ተከሳሽ አቶ ፍቃዱ ዋጋሪ በዐቃቤ ሕግ የቀረበበትን ክስ ክዶ የተከራከረ ሲሆን ወንጀሉም አልፈፀምኩም ሲል መከላከያ ማስረጃዎችን ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል። ሆኖም ተከሳሹ ያቀረባቸው ማስረጃዎች የዐቃቤ ሕግን ማስረጃዎች በአግባቡ ማስተባበል ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱ ትናንት ጥር 20 ቀን 2006 ዓ.ም ጥፋተኛ ነው ብሎታል።
በመሆኑም ተከሳሹ የተጭበረበሩ ሰነዶችን በመጠቀም፤ የሌሎች ሰዎችን ሽንሽን መሬት በማሳየት እና በማሳሳት ፤ የቡራዩ ከተማ ልማት ጽህፈት ቤት መሀንዲስ ሳይሆን ነኝ ብሎ በሀሰት መቅረቡን ዐቃቤ ሕግ ዘርዝሮ፤ ይህንንም ባያያዛቸው ሰነዶችና ባቀረባቸውምስክሮች በኩል ለከፍተኛው ፍርድ ቤት አስረድቷል።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 16ኛ ወንጀል ችሎትም የሁለቱን ወገኖች ክርክር ሲያደምጥ ቆይቶ በትናንትናው ዕለት ተከሳሹን ጥፋተኛ ነው ካለ በኋላ የግራ ቀኙን የቅጣት ማክበጃ እና የቅጣት ማቅለያ በማድመጥ የቅጣት ውሳኔውን ለማስተላለፍ ለጥር 23 ቀን 2006 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
Image
Posted by Addisu Wond.

Advertisements

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: