addisnews

I'm standing for real freedom. I regard freedom of expression as the primary right without which one can not have a proper functioning democracy.

የመኖሪያ ፈቃድ – ከራስ ወዳድነት ያልራቀው የስደተኞች የመጨረሻ ግብ

በሳዑዲ ለተፈናቀሉና ለተጎዱ ዜጎች የእንድረስ ምክክር በኦስሎ

ከራሳቸው አልፎ ባህር ውስጥ ቢደፉት የማይጎድል ሃብት አላቸው። ከሃብታቸው ብዛት የተነሳ ተጨማሪ የነዳጅ ክምችት አግኝተው ጉድጓድ ለመቆፈር ተቃውሞ በመነሳቱ ሪፈረደም አካሂደዋል። ከነዳጅ ይልቅ ውሃ ውስጥ ያለው ህይወት አንደሚብስባቸው በማስታወቅ ድምጽ የሰጡ በመብዛታቸው ነዳጁ ባለበት እንዲቆይ ተወስኗል። ይህ ዜና በተሰማበት ሰሞን ያልተገረመ አልነበረም። ሃብት ካለ ምን ችግር አለ? አንግዲህ እንደዚህ “ብር ይብቃን፤ አሳና የባህር ውስጥ ፍጡራን እንቁራሪትን ጨምሮ ይበልጡብናል” የተባለባት አገር ኖርዌይ ናት።

በተቃራኒው ደግሞ ብር ካየ የሚገባበትን ጉድጓድ፣ የሚፈጽመውን ጥፋት የማይለካው ኢህአዴግ የሚመራት ኢትዮጵያ ያፈራቻቸው ስደተኞች ኖርዌይን ተጠልለዋል። ከአራት ሺህ በላይ ወገኖች ኖርዌይ በጡረታ መልክ እየቆረሰችላቸው ወይም ስራ እየሰሩ ህይወታቸውን ይመራሉ። በኖርዌይ መወልወያና መጥረጊያ ይዘው ቀን የሚገፉ “ራፐሮች”፣ አዛውንቶችን የሚንከባከቡ ሞግዚቶች፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የስራ እርከን የሚሰሩ ባለሙያዎች አንዲሁም በስደተኞች ካምፕ ተጠልለው የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ወገኖች በየዘርፉ በብዙ መልክ ተመድበው ይኖራሉ።

አብዛኞቹ የመኖሪያ ፈቃድ ባለቤቶች ከፖለቲካ ድርጅቶችና ከሲቪክ ማህበራት በተሰጣቸው የአገልግሎት የድጋፍ ደብዳቤና ክትትል ቢሆንም መልስ ካገኙ በኋላ ወገናቸውን መልሶ ከመርዳት የውሃ ሽታ ሆነው እንደሚቀሩ ይነገራል። “በኢትዮጵያ አምላክ ያዙኝ ልቀቁኝ” በማለት የትግል ችቦ ለኳሽ፣ አቀጣጣይ፣ መሪና አስተናባሪ መስለው የሚፈልጉትን እስኪያገኙ በርተው ስለሚጠፉ በድፍረት የሚነሳ obang 2ጉዳይ ባይሆንም አቶ ኦባንግ ሜቶ አምርረው የተናገሩበት ጉዳይ ነበር። እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ትልቅ ጉዳይ የመኖሪያ ፈቃድ በነበራቸውም ሆነ ባልነበራቸው ወቅት ወገኖቻቸውን፣ አገራቸውን እንዲሁም ቃል ኪዳናቸውን ሳይዘነጉ ባሉበት የዓላማ አለት ላይ ሆነው ስራቸውን የሚሰሩ ምርጦችም የመኖራቸው እውነት ይሆናል።

እንቁራሪትን ጨምሮ ለውሃ ውስጥ ነዋሪዎች በመቆረቆር እኛ ለዘመናት አልከፈትም ያለንን የነዳጅ ጉድጓድ በዘጋችው ኖርዌይ ውስጥ የስደት ማመልከቻቸው ተቀባይነት በማጣቱ እድሜያቸውን በካምፕ ውስጥ የሚያሳልፉ የሰው ልጆች ቁጥር ቀላል አይደለም። ከእጅ ወደ አፍ በሆነች የኪስ ገንዘብ ካምፕ ውስጥ ከሚኖሩትን ወገኖች መካካል ለስነልቦና ችግር የተጋለጡ፣ በችግር ምክንያት በቴዲ አፍሮ “ምን ይዤ ልመለስ…” ዘፈን እያለቀሱ ኑሯቸውን የሚገፉትን ወገኖች ጥቂት አይደሉም። እኒህን ወገኖች አሰባስቦ ለመርዳትም ሆነ ለማወያየት ቢችግርም፣ ችግሩ ሳውዲ እንደደረሰው አይነት ባይሆንም ቸል ሊባል የሚገባው አይሆንም። አቶ ኦባንግ ይህንን ጉዳይ ያነሱት “ራሳችንን አስቀድመን እናክብር” በሚል ነበር። እንደ እሳቸው አባባል ራስን የማክበርና ለራስ የመታመን ችግር የዛሬው የፖለቲካ ቀውስ ውጤትም ነው። ኢህአዴግ ራሳቸውን የማያከብሩትን በመሰብሰብ 22 ዓመት የገዛው ጠንካራ ሆኖ ሳይሆን ራሳቸውን ማክበር ያቃታቸውን በሆዳቸው በመደለል ነው። ዛሬም በስደት ምድር ራስን የማክበርና በነበሩበት ቦታ ያለመገኝት ተራ ብላጣ ብልጥነት አገር ቤት ካሉት ኦህዴድ፣ ብአዴን፣ ደህዴን … በተለየ ቦታ የሚያስቀምጥ አይሆንም።

ባለፈው ቅዳሜ ኦስሎ በተካሄደው ታላቅ ስብሰባ ዋናው ጉዳይ በሳዑዲ አረቢያ አገዛዝ አንጋቾችና አክራሪ ጽንፈኞች አማካይነት ዘግናኝ በደል ለተፈጸመባቸውና ለተፈናቀሉ ወገኖች የእርዳታ ገንዘብና ቁስ ማሰባሰብ ነበር። በዚሁ ስብሰባ ላይ ከኦነግና ከኦጋዴን ነጻ አውጪ ተወካዮች በስተቀር ሁሉም ተገኝተዋል። የተለያዩ የክርስትና ሃይማኖት ተቋማት፣ የእስልምና እምነት ተወካይ፣ የኢህአፓ፣ የኖርዌይ ድጋፍ ሰጪ ፎረም፣ የኖርዌይ የስደተኞች ማህበር፣ ተወካዮች በየተራ ንግግር አድርገዋል። ስብሰባውንና ሃሳቡን በማራመድ ግንባር ቀደሙን ሚና የተጫወተው የዝግጅቱ ባለቤት በኖርዌይ የኢትዮጵያ ስደተኞች ማህበር ሰብሳቢ አቶ ፋሲካ ባደረጉት ንግግር የተጀመረው ስብሰባ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክትር አቶ ኦባንግ ሜቶ ነበሩ።oslo10

አቶ ፋሲካ የኖርዌይ ማህበረሰብ ዘወትር ለሚቀርብለት ጥያቄ አፋጣኝ መልስ እንደሚሰጥ በመጥቀስ አመስግነው የወቅቱን አሳሳቢ ሁኔታ በሚገባ አብራርተዋል። ስቅላት፣ አስገድዶ መድፈር፣ እስር፣ ግድያና ስቃይ እጣ ፈንታቸው ለሆኑት ወገኖች ድምጽ ከመሆን ጀምሮ የተለያዩ የአጋርነት መገለጫ ዝግጅቶች ላይ ማህበራቸው መገኘቱን ያመለከቱት አቶ ፋሲል “ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ ከመሆን አልፈን በቁስና በገንዘብ ልንደጉም፣ አለን ልንል፣ አለንታነታችንን ለመግለጽ ስንነሳ ሰፊ ስራ ሰርተን ነው” በማለት በዕለቱ የተገኙትን የተለያዩ ተቋማት ወኪሎችን አወድሰዋል። የሚሰበሰበውንም ገንዝብ ለግሎባል አሊያንስ በማስረከብ እርዳታው ለወገኖች እንዲደርስ ሰፊ ውይይት መደረጉን ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ ገንዘቡ የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች በመሆኑ የገንዘቡን ባለቤቶች ውሳኔ የሚጠይቅ በመሆኑ ውሳኔውን አክብረው አፈጻጸሙን ተግባራዊ እንደሚያደርጉ በሚመሩት ማህበር ስም አመልክተዋል። በስብሳበው ላይ የተገኙት የፖለቲካ ድርጅቶች “ስለ ኢትዮጵያዊነት የሚያገባቸው ብቻ ናቸው” ሲሉም ገልጸዋል።

በይፋ ለመቋቋም አዲስ 22 ዓመት የፈጀበትና የዛሬ ሁለት ዓመት በይፋ የተመሰረተው የቃል ኪዳን ታቦት የፈውስ አገልግሎት አገልጋይና መሪ የሆኑት ወ/ሮ ሰዋሰው “ዓላማችን የታረዘን ማልበስ፣ የተጠማን ማጠጣት፣ የተራበን መመገብ፣ የታሰረን መጠየቅ በመሆኑ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ምን ማድረግ ይገባኛል በማለት አስብ በነበረበት ጊዜ እንዲህ ያለው ስራ መሰራቱን ሰማሁ። አዲስ ከምንጀምር የተጀመረውን ለምን አንረዳም? በማለት መጣሁ” በማለት መልዕክታቸውን ጀመሩ። መጽሃፍ ቅዱስ እንደሚለው በማለት ወገኖችን ስለመርዳት ያስተማሩት ወ/ሮ ሰዋሰው፣ “ጌታ ኢየሱስ ሲመጣ ይህንን ያህል ጉባኤ ተሳትፌያለሁ። በብዙ ሱባኤ ተግኝቻለሁ … የሚል መልስ አያረካውም” ሲሉ መረዳዳት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። በማያያዝም ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ወገኖቿን ለመርዳት ስትነሳ፣ የፖለቲካ ተቋማት ወገኖቻቸውን ለመርዳት ሲነሱ እየተከታተሉ ማውገዝ አግባብ እንዳልሆነም አመልክተዋል።

ባለፉት 22 ዓመታት የክፋት መንፈስ አገራችንን እንደጎዳት ያመለከቱት ወ/ሮ ሰዋሰው፣ “የጻድቅ አይን ወደ ራሱ ይመለከታል” ተብሎ እንደተጻፈው አሁን ያለው ችግር ሲነጋ በእኛም ላይ መልኩን ቀይሮም ቢሆን ሊከሰት እንደሚችል አመልክተዋል። ሲጨርሱም “በሰው አገር ላይ ነን እኛም ላይ የሚደርሰው አይታወቅም። የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” በማለት ለቀረበላቸው አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የቅዱስ ገብርኤልና አቡነ ተ/ሃይማኖት ቤተክርስቲያንን በመወከል የተናገሩት ወ/ሮ ሂሩት ወርቁ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሁሌም ከልጆቿ ጋር ተለይታ እንደማታውቅ የቀደመው ታሪኳ እንደሚመሰክር አስምረውበታል። አሁንም በተመሳሳይ ይህንኑ በጎ ስራ እንደሚገፉበትና የርዳታው ማሰባበሰብ በቤተክርስቲያን ደረጃ እየተሰራ እንደሆነና የተሰበሰበውንም ገንዘብ በወቅቱ እንደሚያስረክቡ አመልክተዋል። በመጨረሻም ለዚህ በጎ ስራ የተሰማሩትንና ፈቃደኛ የሆኑትን በሙሉ በረከትን ተመኝተውላቸዋል።

oslo 3ከኢትዮጵያ የ7ኛው ቀን አድቬንቲስት ቤ/ክ ህብረት የተወከሉት ዶ/ር ዙፋን አግደው በበኩላቸው ወገኖችን ለመርዳት በተጠራው ስብሰባ ላይ መገኘታቸው እንዳስደሰታቸው አመልክተዋል። በተለያዩ የበጎ ተግባራት ቤተ ክርስቲያናቸው ስትሳተፍ እንደቆየች ያወሱት ዶ/ር ዙፋን “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ታነሳለች በሚል እንደተጻፈው ጸሎታችን አንዲሰማ አንድ መሆን ያስፈልጋል” በማለት በህብረት የመሰባሰቡ ቁልፍ የልብ አንድነት መፍጠር ላይ እንደሆነ ገልጸዋል። “የእግዚአብሔር ቃል ሁለት ያለው ምንም ለሌለው እንዲሰጥ ያዛልና በርዳታው በኩል ነቅተን እንሳተፋለን” ሲሉ የወከሉትን ቤ/ክ አቋም አንጸባርቀዋል።

የኢህአፓ ተወካይ አቶ ምናሴ “ለዚህ ሁሉ አሳፋሪና አንገት የሚያስደፋ የወገኖቻችን ስቃይ ተጠያቂ ወያኔ ነው” ሲሉ የችግሩን ግዝፈት አመልክተዋል። የዲሞክራሲ ለውጥ ድጋፍ በኖርዌይ ተወካይ አቶ አቢ አማረ በተመሳሳይ የችግሩን አሳሳቢነትና አገር ቤት ስልጣንን በሃይል ያዘውን የኢህአዴግ አገዛዝ እጅ ለእጅ በመያያዝ መታገል በዋናነት አስፈላጊ መሆኑንን ጠቁመው በሳዑዲ አረቢያ ለተፈናቀሉ በሚደረገው ድጋፍ ላይ ድርጅታቸው የዘወትር ድጋፉን እንደሚገፋበት አረጋግጠዋል። በድርጅት ያልታቀፉ በድርጅት ጥላ ስር እንዲደራጁ ጥሪ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ ስደተኞች ማህበር ተወካይ አቶ ሃምሳሉ በበኩላቸው ተመሳሳይ የትብብር ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ የጋራ መድረክ ፎረም በኖርዌይን በመወከል ወ/ሮ ዙፋን አማረ ሲናገሩ “አንዳንዴ  ምነው በአባቶቼና በአያቶቼ ዘመን ምነው በተፈጠርኩ እላለሁ” በማለት የቀድሞው ዘመን ኢትዮጵያዊነትን ከአሁኑ ዘመን አንገት አስደፊው ማንነታችን ጋር አዛምደው ተናግረዋል። ይህ ትውልድ እጣው ውርደት እንደሆነ ያመለከቱት ወ/ሮ ዙፋን፣ ከዚህ ውድቀትና ሃፍረት ላይ ከጣለን ስርዓት እስከወዲያኛው ነጻ ለመውጣት እሳቸው ወከሉት ድርጅት እየሰራ መሀኑንና የሁሉም ህብረት አስፈላጊ መሆኑንን አስታውሰዋል።

“የቁርጥ ቀን ልጅ፤ የኢትዮጵያ እውነተኛ ልጅ፣ ንጹህ ኢትዮጵያዊ፣ ኢትዮጵያዊያን በተቸገሩበት ቦታ ሁሉ ቀድሞ የሚደርስ፣ …”፤ “የጥቁሩ ሰው” ስም ኦባንግ ሜቶ ተባለ። ኦባንግ ተነሱ። አስቀድመው ንግግር አድርገው የነበሩትን ሴት እህቶች “አከብራለሁ” አሉ። በመቀጠል በሳዑዲ ወገኖቻችን ላይ የደረሰውን ጉዳይ አስረዱ። በመቀጠልም ንግግራቸውን ወደ ስደተኛው አዞሩት “ፎቶ ከኔ ጋር ትነሳላችሁ፤ መልስ ስታገኙና የመኖሪያ ፈቃድ ስታገኙ አትታዩም፤ ትጠፋላችሁ” በማለት ፊት ለፊት ወቀሳቸውን ሰነዘሩ። በመሪነትና አቅጣጫን በሚያመላክት ሞገስ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት አቶ ኦባንግ “ድክመት አለባችሁ” ብለዋል።

በኖርዌይ የመኖሪያ ፈቃድ ተከልክለው በስደት ካምፕ ውስጥ ያሉት ወገኖች በምን ደረጃ እንዳሉ አስታወቁ። የአእምሮ፣ የስነልቦናና የኢኮኖሚ ችግር እየተፈራረቀባቸው ዓመታት አንድ ቦታ ተቀምጠው መኖራቸው “እንዴት እረፍት ይሰጣል” ሲሉም ጠየቁ። “እናንተ ትናንት በተመሳሳይ ችግር ላይ የነበራችሁ፤ ዛሬ ወረቀት ስላገኛችሁ የቀድሞውን ማንነታችሁን ረሳችሁ” ሲሉ ሲሳካላቸው የሚሸሹትንና ወገኖቻቸውን የሚዘነጉትን አወገዙ። ከአጠቃላይ የወቅቱ ችግር ጋር በማያያዝ ‘ሰዎች ንን ራሳችንን እናክብር። አሁን የሚታዩት ችግሮች በሙሉ ራስን የማክበር ችግር ነው። እባካችሁን ራሳችሁን አክብሩ” ሲሉ መከሩ።

“ወያኔዎች ስራቸውን ያወቃሉ። እኛ ግን ስራችንን አናውቅም። በረሃ ሲገቡ ትግራይን ነጻ ለማውጣት ነበር ። እኔንና እናንተን የሚመስሉት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ራሳቸውን ማክበር ባለመቻላቸው ለትንሽ ዳቦ ጫካ ውስጥ የገቡት ወያኔዎች ትልቁን ዳቦ አገኙት” ሲሉ ከላይ ያነሱትን ሃሳብ አብራሩ። በስደት ኖርዌይ ከመጡ በኋላ ኦስሎን አንኳ የማያውቁ ወገኖችን ጉዳይ ደጋግመው ያነሱት አቶ ኦባንግ “እኔ ብለን ስንጀምር ነገር ይበላሻልና እኛ ብለን እንጀምር” ሲሉ ስለ ብሔር መከፋፈል ጣጣ መልዕክት ሰጥተዋል።obang 1

“አዲሲቷን ኢትዮጵያ ስንገነባ ሁሉን አስረን አንችልም። ዓለማችንም አይደለም” ያሉት ጥቁሩ ሰው፣ የስደት ምድር ጊዚያዊ ማረፊያ እንጂ የዘላለም አገር አይደለምና የራሳችን አገር ባለቤት ለመሆን በውስጣችን ያለውን ተንኮል እናስወግድ ብለዋል። በነጻነት እቅዳችን ውስጥ የሚበድሉንን ጨምሮ ሁሉንም ነጻ የማውጣት ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑንን ያወሱት ኦባንግ ሜቶ “በሳዑዲ የሌሎች አገራት ዜጎች መንግሥታቸው ሲሰበስባቸው የእኛ ዜጎች ግን እንደ ቅያሪ ጎማ በሌላ ይተካሉ በሚል ወገንና አገር አልባ እንደሆኑ ተቆጥረዋል። ከዚህ በላይ የከፋ ውርደት የለምና አሁንም በድጋሚ የምነግራችሁ ራሳችሁን በማክበር ለወገናችሁ ምላሽ ስጡ” በማለት የፊልም ምሳሌ በመስጠት ንግግራቸውን አጠቃለዋል።

“ይህ ፊልም የወኖቻችን ስቃይ የተቀረጸበት ነው። ፊልሙ ብርሃን የያዘውን ምስል ለመመልከት ብርሃን ይፈልጋል። ፊልሙ ብርሃን ካላገኘ ምስሉ ሊታይ አይችልም። ብርሃን ከላገኘ በጨለማ ውስጥ እንዳለ ይቀራል። እናንተም በጭለማ ውስጥ ላሉት ወገኖቻችሁ ብርሃን መሆን አለባችሁ። አገራችን ብርሃን የሚሆኑላት ትፈልጋለችና!!” አቶ ኦባንግ የስደተኞችን ጉዳይ በመያዝ አግባብ ካላቸው የኖርዌይ ባለስልጣናት ጋር ተነጋግረዋል። አቶ ኦባንግ በሚቀጥለው ወር ከኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር በቀረበላቸው የውይይት ጥያቄ መነሻነት ወደ ኖርዌይ ተመልሰው ይመጣሉ ። አቶ ኦባንግ ባለፉት ስድስት ወራት በድርጅታቸው አማካይነት ስለሰሩት ስራና አጠቃላይ እንቅስቃሴ አስመልክቶ ከጎልጉል ጋር ሰፊ ቃለ ምልልስ እንደሚያደርጉ ቃል በመግባት የሚከተለውን ተናግረዋል። “አሁን ነገሮች መልክ የያዙበት ወቅት ላይ እየተቃረብን ነው። ዜጎች ራሳችሁን በማክበርና ከክፋት ልቡናቸውን በማጽዳት ይደግፉን። የተቀረውን እኛ እንሰራዋለን፡፡”

Source/www.gooulgul.com

Advertisements

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: