addisnews

I'm standing for real freedom. I regard freedom of expression as the primary right without which one can not have a proper functioning democracy.

ሰሞኑን በጣለው ከፍተኛ ዝናብ የመገናኛ ድልድይ መሠረት ጉዳት ደርሶበታል

ll
-ድልድዩ ላልተወሰነ ጊዜ ለትራፊክ ዝግ ሆኗል

-የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣንና የባቡር ኮርፖሬሽን ውዝግብ አልተፈታም

ሐምሌ 30 ቀን 2006 ዓ.ም. አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የጣለው ዝናብ በመገናኛ ድልድይ መሠረት ማጠናከሪያ (ኃይል) ላይ የመሸርሸር ጉዳት በማስከተሉ ምክንያት፣ ድልድዩ ለትራፊክ ዝግ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፍቃዱ ኃይሌ ባለፈው ዓርብ በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ፣ ረቡዕ ሐምሌ 30 ቀን በአጭር ደቂቃ ውስጥ የጣለው ዝናብ በተጠቀሰው የመገናኛ ድልድይና በሌሎች ስድስት ቦታዎች ላይ ጉዳት ማስከተሉን ገልጸዋል፡፡ የጣለው ከባድ ዝናብ ያልተለመደ መሆኑን የገለጹት ኢንጂነሩ፣ ከኢትዮጵያ ሚትዎሮሎጂ በተገኘ መረጃም 30 ሳንቲ ሜትር ከፍታ እንደነበረው አስረድተዋል፡፡

በዝናቡ ምክንያትም በበርካታ የአዲስ አበባ አካባቢዎች የጐርፍ መጥለቅለቅ መከሰቱን፣ በመንገድ መሠረተ ልማቶች ላይም ጉዳት መድረሱንም ኢንጂነር ፍቃዱ ገልጸዋል፡፡

ቦሌ መድኃኔዓለም፣ አያት አካባቢ፣ ካሜሩን ኤምባሲ፣ ቦሌ ወሎ ሠፈር፣ ካራማራ ድልድይ፣ ከጉርድ ሾላ ቴሌ፣ ከካራ ማዕድን ሚኒስቴር፣ ሣህሊተ ምሕረት አካባቢ ከፍተኛ የጐርፍ መጥለቅለቅ እንደደረሰባቸውና በመሠረተ ልማት ላይም ጉዳት ማስከተሉን ኢንጂነር ፍቃዱ ገልጸዋል፡፡

የጐርፍ ማስወገጃ ቦይ ጠባብ መሆን፣ የዲዛይን ችግር፣ አዲስ አበባ ተራራማ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ከተራራ አካባቢ የሚመጣውን ጐርፍ ተቀብሎ የሚያስተናግድ መሠረተ ልማት አለመኖር፣ የባቡር ፕሮጀክቱ ከሚፈጥረው ችግር ውጪ ለሰሞኑ ጐርፍ እንደ ምክንያት የተጠቀሱ ናቸው፡፡

የሰሞኑ ጐርፍ የመገናኛ ድልድይ መሠረቱ እንዳይንሸራተት የተገነቡ ደጋፊ ምሶሶዎች መካከል የተወሰኑት ያረፉበት ቦታ መሸርሸሩን ኢንጂነሩ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ድልድዩ ያረፈበት ምሰሶ መሠረት በመንቀጥቀጥ ምክንያት እንዳይንሸራተትና ድልድዩ እንዳይደረመስ በማለት ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ ለትራፊክ ዝግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የምሕንድስና ባለሙያዎች በመገናኛ ድልድይ አካባቢ ያለው የግንባታ ሒደት ለአደጋ የተጋለጠ እንደሆነ የጠቆሙ ሲሆን፣ በአካባቢው የሚደረገው ግንባታ የቀድሞውን የመገናኛ ድልድይ መሠረት የሸረሸረና በአካባቢው ከፍተኛ ማሽነሪዎች በሥራ ላይ በመሆናቸው የሚፈጥሩት መንቀጥቀጥና ድልድዩ ለትራፊክ ክፍት ሆኖ ከሥር ደግሞ ግንባታ መካሄዱ ተገቢ እንዳልሆነም አስረድተዋል፡፡

በመገናኛ ድልድይ ሥር የሚደረገው ከፍተኛ የሆነ ጥልቅ ቁፋሮና ከላይ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ በድልድዩ ላይ መሰንጠቅን፣ እንዲሁም ዋናው የድልድዩ መሠረት በግንባታ በመቆፈሩ ምሰሶው እንዲሸሽ ምክንያት ሊሆን ስለሚችልም ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡

በጉዳዩ ላይ የተጠየቁት ኢንጂነር ፍቃዱ፣ ‹‹አማራጭ የሌለው ነገር ነው፤›› በማለት ነው ምላሽ መስጠት የጀመሩት፡፡ ‹‹የቀድሞው›› ድልድይ ምሰሶ የቆመበት መሬት ዙሪያ ሲቆፈር መሬቱን ያናጋል፡፡ መናጋቱ ጉዳት እንዳያደርስ ሌላ ደጋፊ ግድግዳ (ፓይል) ነው የተሠራው፡፡ ይህ ድንገት መሬቱን ገፍቶ እንዳይወድቅ በሚል ነው የተሠራው፤›› ብለዋል፡፡

በማከልም ‹‹በበቀደሙ ዝናብ ዳር ላይ ያሉት ደጋፊ ኮንክሪቶች በመሸርሸራቸው እንዲሁም ቫይብሬሽኑ (መንቀጥቀጡ) ስላለ እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ለትራፊክ ዝግ እንዲሆን አድርገናል፤›› ብለዋል፡፡

መጀመሪያውንም ግንባታው ሲካሄድ ከሦስት ቶን በላይ ክብደት ያለው ተሽከርካሪ እንዳያልፍ ምልክት ቢቀመጥም ሊከበር አለመቻሉን የገለጹት ኢንጂነር ፍቃዱ፣ በአሁኑ ወቅት አቃፊ ግድግዳ እየተገነባ በመሆኑ እስከዚያው ድረስ ዝግ እንዲሆን መደረጉን አብራርተዋል፡፡

‹‹አቃፊ ግድግዳው ከተገነባ ሥጋቱ ይቆማል፤›› ያሉት ኢንጂነር ፍቃዱ፣ ‹‹ድልድዩ ይነቃነቃል፡፡ በእኔ እምነት ግን መነቃነቁ ጉዳት አለው ማለት አይደለም፡፡ ድልድይ ሲሠራ እንዲወዛወዝ ተደርጐ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ቀላል የባቡር ፕሮጀክት ጋር ያላቸውን አለመግባባት በተመለከተ የተጠየቁት ኢንጂነር ፍቃዱ፣ ‹‹ከባቡር ፕሮጀክቱ ጋር የተያያዙትን መንገዶች ከመምራት ጋር የተያያዘ ችግር አለ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ያለምንም ዝግጅትና ዕውቀት ነው የአስፋልት መንገድ የሚቆርጡት፣ በቅንጅትም ለመሥራት ፈቃደኛ አይደሉም፤›› የሚሉት ኢንጂነር ፍቃዱ፣ ‹‹የባቡር ኮርፖሬሽን ቦርድ አባል ሆኜ እንዲህ የተቸገርኩኝ እዚያ ውስጥ ያልገባ ሰው ቢሆን ኖሮ ምን ይደረጋል?›› ሲሉ ጥያቄውን በጥያቄ መልሰዋል፡፡

‹‹እግረኞች በየት ነው የሚያቋርጡት? መሸጋገሪያ ድልድይ ይኑር አይኑር በሚለው መግባባት አልቻልንም፤›› ብለው፣ የሰሞኑ ጐርፍ ከፊል ምክንያትም የባቡር ፕሮጀክቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ጐርፉ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ መፍሰስ ይችላል፡፡ አሁን ግን የባቡር ፕሮጀክቱ ምንም ዓይነት የውኃ ማስወገጃ ሳይተው ግድግዳ በመገንባቱ ውኃው ማለፍ አልቻለም፤ ብለዋል፡፡

‹‹የባቡር ፕሮጀክት ሠራተኞች የባቡር መስመር መሥራት ነው እንጂ የሚችሉት መንገድ አይችሉም፡፡ ስለዚህ መንገዱ ለባለቤቱ ይሰጥ በሚል እየተነጋገርን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ከአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ መረጃ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

Advertisements

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: