addisnews

I'm standing for real freedom. I regard freedom of expression as the primary right without which one can not have a proper functioning democracy.

የመለስ ዜናዊ ምስል በገንዘብ ላይ?!

Image

አንዳንዴ ወሬ በባዶ ሜዳ ይናፈሳል። ብዙ ጊዜ ትንሽ ጫፍ ይዞ ይናፈሳል። የህወሓት መንግስትን በተመለከተ አያደርጉም የምለው ነገር ስለሌለ ለመጠራጠሬ ገደብ አብጂቸ ነው የምጠራጠረው። ብዙ ጊዜ ግን ስለነሱ የሚወራውን አልጠራጠርም። ያደርጉታል።

ሰሞኑንን (ምናልባት ሌሎቻችሁ ከሰማችሁ ቆይታችሁ ይሆናል!) የህወሓት መንግስት የአመስት መቶ ብር ኖት የማዘጋጀት ሃሳብ እንዳለው እና በገንዘቡ ላይ የ “ባለ ራዕዮ መሪ” ምስል እንደሚያርፍበት ሰማሁ። የታላላቅ መሪዎችን ምስል በምንዛሬ ላይ ማስቀመጥ አዲስ ነገር አይደለም። ጥያቄው ግን ታላቅ ማነው? ታላቅነቱ እንዴት ነው? በየትኛውም ማህበረሰብ የበቀሉ የፖለቲካ መሪዎች የራሳቸው የሆኑ ተቃዋሚዎች እንደሚኖራቸው እሙን ነው። ነገር ግን ከሚከተሉት ፖሊሲ በመነሳት ዜግነታቸው ጭምር ጥያቄ ውስጥ የገባ እና በእኛ ሃገር ዘይቤ በባንዳነት ሂሳብ የተያዙ የሌሎች ሃገር መሪዎች ያሉ አይመስለኝም። ያውም ምስላቸው ምንዛሬ ላይ የሚወጣ?! ፈጽሞ አይመስለኝም። የቻይናው ማኦ የጠባብ ብሔርተኛ የፖለቲካ መሪ አልነበረም። የዘር ትምክህት አባዜ አልነበረውም። የኢንዶኔዢያው ሱካርኖ እንደዚያው። የፓኪስታኑ መሃመድ አሊ ጂና እንደዚያው። ብዙ የ”ሶስተኛውን ዓለም” ሃገሮች መሪዎች ለአብነት ማንሳት ይቻላል።

የመለስ ዜናዊ ታሪክ ሌላ ነው( ለማን ይተረካል እንጂ!)። የመራውን የፖለቲካ ቡድን ለይስሙላም ቢሆን ሃገራዊ መልክ ሳይሰጠው የህወሓት ሊቀመንበር እንደሆነ ነው የሞተው። ከዚያ በላይ ግን የመለስ ዜናዊን የጎሰኛነት ጠባይ ትግራይም አዲሳባም ላይ ሆኖ የተናገራቸው የተለያዮ ንግግሮች የሚመሰክሩት አንድ ነገር ነው፡- የመለስ ዜናዊን ከልክ ያለፈ ጎጠኛነት። ምንም ጥያቄ የለውም ህወሃት ውስጥ አብረውት ብዙ ዓመት የፖለቲካ ስራ ለሰሩ፣ታገልን ለሚሉ ጓደኞቹ መለስ ዜናዊ ሌላ ሰው ነበር-ምንም እንኳን አንዳንዶች ጉደኞቹ ከጊዜ በኋላ ቢቀየሙትም (ወይንም የተቀየሙት ቢመስሉም)። እነዚህ የሚወዱት ጓደኞቹ ከፈለጉ የወርቅ ሃውልትም ሊያቆሙለት ይችላሉ ( ለባለ “ራዕዮ” መሪያቸው ያልሆነ ግዳይ ምን ይፈይዳል ታዲያ!)

ነገር ግን ማወቅ ያለባቸው ጉዳይ እንደው በህወሃትኛ ቋንቋ እንኳን መለስ ዜናዊ ለጉራጌው ምኑ ነው?? በአማራው ምኑ ነው? ለኦሮሞው ምኑ ነው? ለወላይታው ምኑ ነው? እያለ እያለ ይቀጥል እና አጥብቆ ጠያቂ ከመጣ ደሞ “እንኳን ለሌላው ለተምቤኑ ምኑ ነው?” ጥያቂ ሊነሳም ይችላል።

መለስ ዜናዊ ትልቁን ከሃዲ እና ጎጠኛ ነበር የሚለውን ነጥብ ትተን በትንሹ አወዛጋቢ የሚባል የፖለቲካ ሰው ነበር። ህወሓት ይሄን አላውቅም ካለ ፓለቲካ አያውቅም ሊያስብለው ይችላል። እውነቱ ይሄ ሆኖ እያለ ህወሓት የመንግስት ስልጣን ስለያዘ ብቻ እንደፈለኩ ገንዘብ ላይ የመለስ ዜናዊ ምስል አትማለሁ ቢል የህወሓትን የአክራሪነት ስሜት ከሚጠቁም በስተቀር ትርፍ ያለው ነገር አይመስለኝም። ከህወሓት ጋር አብሮ የሚሞት የገንዘብ ኖት ነው የሚያዘጋጀው ማለት ነው። ምናለበት ህወሓት ለጎጠኝነቱ ለከት ቢያበጂለት?! ህወሓት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ምንድን ነው የሚፈልገው?? ሌልቹስ “እህት” ነን የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዴት ይሄን ጉዳይ በቸልታ ይመለከታሉ?!

የመለስ ዜናዊ ምስል በምንዛሬ ላይ የመውጣቱ ነገር በትክክል ሊደረግ ታስቦ ከሆነ ክህወሓት በላይ ተጠያቂ የሚሆኑት ክህወሓት ጋር እየሰሩ ያሉ ድርጂቶች ናቸው!
source Borkena.com

Single Post Navigation

Leave a comment