addisnews

I'm standing for real freedom. I regard freedom of expression as the primary right without which one can not have a proper functioning democracy.

አሜሪካን ያስበረገገው ግድያ

vv
በዋሽንግተን ዲሲ እምብርት በሚገኘው የአሜሪካ በባህር ኃይል ቅጥር ግቢ ውስጥ ተኩስ ከፍቶ 12 ሰዎችን የገደለው የቀድሞ የባህር ኃይል ባልደረባ ተገደለ፡፡

አሮን አሌክሲስ የተባለው ግለሰብ ከገደላቸው በተጨማሪ ሰላሳ ሰዎችን አቁስሏል፡፡ ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግለትና ሦስት ሺሕ የሚደርሱ ሠራተኞች በሚንቀሳቀሱበት ቅጥር ግቢ ውስጥ የደረሰው ጥቃት እ.ኤ.አ. በ2009 በአሜሪካ ቴክሳስ በሚገኘው የባህር ኃይል ቤዝ ውስጥ በሠራተኞች ላይ ከደረሰው ግድያ ወዲህ አስከፊው ነው ተብሏል፡፡

ከፖሊሶችና ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በተደረገው የተኩስ ልውውጥ የ12ቱ ሰዎች ገዳይ አሮን አሌክሲስ በመገደሉ የሟቾች ቁጥር 13 ደርሷል፡፡ በባህር ኃይል ቅጥር ግቢ ውስጥ ለምን ተኩስ መክፈት እንዳስፈለገው የተለያዩ መረጃዎች ቢኖሩም፣ በቡዲዝም እምነቱ ምክንያት በባህር ኃይሉ ኃላፊዎች መገለል እንደደረሰበት መናገሩ ተሰምቷል፡፡

ባለሥልጣናት ለግድያው ያነሳሳውን መንስዔ እያጣሩ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ደግሞ የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ በማዘዝ ድርጊቱን ‹‹አረመኔያዊ›› ብለውታል፡፡ ድርጊቱን ያወገዙት ፕሬዚዳንት ኦባማ አሜሪካውያን በተደጋጋሚ እያጋጠማቸው ላለው የጦር መሣርያ ጥቃት መፍትሔ ሊሰጡ ባለመቻላቸው እየተወገዙ ነው፡፡ በተለይ አሜሪካውያን የጦር መሣርያ መታጠቅ መብታቸው እንዲገደብ በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በተደጋጋሚ የተጠየቀ ቢሆንም፣ እገዳውን ዕውን ለማድረግ አልቻሉም፡፡ መሣርያ የታጠቁ አሜሪካውያንም ሌሎችን መግደላቸውን ቀጥለዋል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2007 ጀምሮ በፎርት ዎርዝ የሎጂስቲክስ ድጋፍ ሠራተኛ በመሆን ባህር ኃይሉን የተቀላቀለው የ34 ዓመቱ አሌክሲስ እ.ኤ.አ. በ2010 ከጦር መሣርያ ጋር የተያያዘ ጥፋት በመፈጸሙ ታስሮ ነበር፡፡ ኤፍቢአይም ግለሰቡ ከመሣርያ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ባለፉት አራት ዓመታት ሁለት ጊዜ መታሰሩን አስታውቋል፡፡

በዋሽንግተን ዲሲ የፖሊስ አዛዥ የሆኑት ካቲ ላኒየር አሌክሲስ ባይገደል ኖሮ በርካቶችን ሊገድል ይችል ነበር ብለዋል፡፡

የባህር ኃይሉን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፕሮጀክት ከሚሠራው ሒውሌት ፓካርድ ሥራዎችን ወስዶ ለሚሠራው ‹‹ዘ ኤክስፐርትስ›› ተቀጣሪ የነበረው አሌክሲስ ከፍተኛ ጥበቃ ወደሚደረግለት ባህር ኃይል ቅጥር ለመግባት የኮምፒውተር ድርጅቱን መታወቂያ ተጠቅሞ ሊሆን ይችላል ቢባልም የተረጋገጠ ነገር የለም፡፡ ሆኖም ሦስት ሺሕ የሚጠጉ ሠራተኞች ባሉበትና የአሜሪካ ባህር ኃይልና ሰርጓጅ መርከቦችን የመግዛት፣ የማደራጀትና ሲስተሙን የመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው የባህር ኃይል ሲስተም መምርያ ዋና ቢሮ በሚገኝበት ሕንፃ ውስጥ በመግባት 12 ሰዎችን መግደል ችሏል፡፡ በወቅቱም ኤአር 15 የተባለ መሣርያ፣ በተኩስ ልውውጥ ወቅት ከፖሊስ የቀማውን ሽጉጥና ሌላም አንድ መሣርያ ታጥቆ ነበር፡፡

በባህር ኃይሉ ቅጥር በሕንፃ ቁጥር 197 ውስጥ በሚገኘው ካፍቴርያ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ሰዎች ቁርስ እየተመገቡ ባሉበት ከጠዋቱ 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ላይ ነበር መሣርያ የታጠቀው አሌክሲስ ወደ ካፍቴሪያው መተኮስ የጀመረው፡፡ ተኩሱን ሲከፍትም ሊታይ ከማይችልበት ሥፍራ ሆኖ እንደነበር ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

አሌክሲስ ከዚህ ቀደም ከጦር መሣርያ ጋር በተያያዘ ሁለት ጊዜ ያህል ቢታሰርም በግድያ ወንጀል ተጠርጥሮ አያውቅም፡፡ ይልቁንም የሲያትል ፖሊስ ስለ አሌክሲስ የገለጸው፣ አሌክሲስ በአሜሪካ እ.ኤ.አ. በ2001 በተከሰተው የ9/11 አሸባሪዎች ጥቃት የተጐዱ ሰዎችን ለማትረፍ በተደረገው ርብርብ ጉልህ ተሳትፎ እንደነበረው ነው፡፡ አሌክሲስ ሰኞ ሌሊት በባህር ኃይሉ ቅጥር ውስጥ ጥቃት ከፈጸመና ከተገደለ በኋላ አባቱ ለመርማሪ ፖሊሶች እንደተናገሩት፣ ደርሶበት በነበረ ጭንቀት ብስጭትን በሰላማዊ መንገድ የማስተናገድ ችግር ነበረበት፡፡

አሌክሲስ በኤሮናቲክስ ኢንጂነሪንግ ዲግሪ አለው፡፡ የቡዲዝም እምነት ተከታይ ሲሆን ፍላጐቱም መነኩሴ መሆን እንደነበር ጓደኞቹ ለአሶሼትድ ፕሬስ ተናግረዋል፡፡

በ9/11 የሽብር ጥቃት የደረሰባቸውን ለመታደግ ተሳታፊ የነበረው አሌክሲስ ድርጊቱን የፈጸመው ከሽብር ጋር በተያያዘ ስለመሆኑ የተገኘ መረጃ የለም፡፡ የዋሽንግተን ዲሲ ከንቲባ ቪንሰንት ግሬይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም አሌክሲስ ያደረሰው ጥቃት ከሽብርተኝነት ጋር የተያይዘ ስለመሆኑ መረጃ አለመገኘቱን ነው፡፡ በሌላ በኩል ገዳዩ ከዚህ ቀደም የአዕምሮ ኹከት እንደነበረበት አንዳንድ መረጃዎች እየወጡ ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2009 ቴክሳስ ባለው በፎርት ሁድ የባህር ኃይል መደብ ሜጀር ናዲሊ ሐሰን የተባለ የሥነ ልቦና ሐኪም 13 የሥራ ባልደረቦቹን ሲገድል አሜሪካ በኢራቅና በአፍጋኒስታን የምታካሂደውን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ተቃውሞ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ተሰጥቶ ነበር፡፡ የአሌክሲስንም ጥቃት ከዚሁ ጋር በማነፃፀር አሜሪካ በሶሪያ ላይ ወታደራዊ ዕርምጃ እወስዳለሁ በማለቷ ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚል ግምት እየተሰጠ ነው፡፡

ዘግይተው የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ጥቁር በመሆኑ ምክንያት ብቻ ዕድገት መነፈጉን ይገልጽ ነበር፡፡ ነገር ግን መርማሪዎች ከአሌክሲስ ግድያ በስተጀርባ ያሉ ምክንያቶችን ለማወቅ የተለያዩ የመረጃ ቁርጥራጮችን እየሰበሰቡ መሆኑ ታውቋል፡፡ ለጊዜው ባለሥልጣናት ከግድያው ጀርባ ያለውን ምክንያት አለማወቃቸውን ነው እየገለጹ ያሉት፡፡ የቡዲዝም አጥባቂ አማኝ የነበረው አሌክሲስ ለምን እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት እንደፈጸመ በምርመራው ሒደት እስከሚጣራ ድረስ ዝርዝር መግለጫ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ ድርጊቱ ግን አሜሪካውያንን አስበርግጓል፡፡

ethiopian reporter

Single Post Navigation

Leave a comment