addisnews

I'm standing for real freedom. I regard freedom of expression as the primary right without which one can not have a proper functioning democracy.

Archive for the day “October 5, 2013”

በሙስና ከተጠረጠሩ ግለሰብ 7 ሚሊዮን ጥሬ ብር ተያዘ

mnn
ኢሳት ዜና:በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት የአዳማ ጉምሩክ የህግ ማስከበሪያ ሀላፊ ከነበሩት ግለሰብ ሰባት ነጥብ አራት ሚሊዮን ጥሬ ገንዘብ መያዙን የፌደራል ስነ ምግባር ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ገለጹ፡፡
ሀላፊ የነበሩት አቶ ተመስገን ስዩም 12 የነዳጅ ማመላለሻ ቦቴዎችን በሌላ ሰው ስም ገዝተው ለተገዙት መኪኖች ውክልና በመውሰድ መኪኖቹን ለሌሎች ሰዎች ሸጠዋል የሚል መረጃ ቀርቦባቸዋል፡፡
ከመኪናዎቹ በተገኘ የሽያጭ ገንዘብ ደግሞ ሁለት ዶዘሮችን ለመግዛት ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ለአንድ ድርጅት ክፍያ እንደፈጸሙ ተገልጿል፡፡
ግለሰቡ ክፍያ ከፈጸሙባቸው ዶዘሮች መካከል አንዱን በ7.6 ሚሊዮን ብር ለአንድ ድርጅት ያከራዩ ሲሆን ሌላውን 7.4 ሚሊዮን ብር የሚያወጣውን ዶዘር ለመረከብ በዝግጅት ላይ እንደነበሩ መረጃ መገኘቱን የመንግስት መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል፡፡
ከግለሰቡ ወንጀል ጋር ተሳትፎ ነበራቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሁለት ነጋዴዎች ከ14 ቀን በፊት በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ገንዘቡንና ንብረቱን ከሙስና ጋር የተያያዘ ነው በሚል ጥርጣሬ ግለሰቡ አንድ ዶዘር የገዙበት 7.4 ሚሊዮን ብር ከተገዛበት ድርጅት እንዲመለስ ተደርጎ ኮሚሽኑ የተረከበ ሲሆን ሌላው 7.6 ሚሊዮን ብር የሚያወጣው ዶዘር እንዲታደግ ተደርጓል፡፡
አቶ ተመስገን በፖሊስ ሲፈለጉ ከቆዩ በኋላ ከአዲስ አበባ ወደ ጋምቤላ በመሸሽ ወደ ደቡብ ሱዳን ለመግባት ሲሉ መያዛቸው ታውቋል፡፡

የአባይ ግድብ መሰረቱ ችግር ሊኖረው ይችላል ተባለ

jk
ኢሳት ዜና :- ብሉበርግ የአለማቀፍ አጥኚዎች ቡድንን ዋቢ በማድረግ እንደዘገበው መንግስት በማስገንባት ላይ ያለው የአባይ ግድብ መሰረቱ ችግሮች ሊኖሩበት ስለሚችል መንግስት እንደገና እንዲያስጠና መክሯል።

ግድቡ በታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች ላይ የሚያስከትለው ጉዳት በደንብ መጠናት አለበት ሲሉ የባለሙያዎቹ ቡድን አስተያየቱን ሰጥቷል።

የግድቡን መሰረት ለማጠንከር መሰረታዊ የሆነ ለውጥ ያስፈልጋል በማለት ያመለከቱት ባለሙያዎች፣ “ድክመት ቀጠና “ ተብሎ በተለየው አካባቢ ያለው ድንጋይ እንደገና ሊፈተሽ እንደሚገባው መክረዋል።

ይህ የጥናት ቡድን በኢትዮጵያ ሀሳብ አመንጭነት የተቋቋመ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ፣ ከግብጽና ሱዳን ሁለት ሁለት ባሙያዎች ከሌሎች አገራት ደግሞ አራት ባለሙያዎች ተካተውበታል። እስካሁን ይፋ ያልወጣው ሪፖርት ለሶስቱ መንግስታት መላኩንም ብሉምበርግ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ ቀደም የጥናት ቡድኑ ያቀረበው ሀሳብ ግድቡ ምንም ጉዳት እንደማያመጣ ያረጋገጠ ነው በማለት ይፋ ማድረጋ ይታወሳል።

አሁን የቀረበው አዲስ ጥናት ግን ግድቡ የግብጽን የውሀ አቅርቦትና የሀይል አቅርቦት የሚቀንስ መሆኑን የሚያመለክት ነው።

የጥናት ቡድኑ ያቀረባቸውን አስተያየቶች ኢትዮጵያ ትቀበላቸው አትቀበላቸው እንዲሁም ስራው ተቋርጦ እንደገና ጥናት ይካሄድ አይካሄድ በዘገባው የተጠቀሰ ነገር የለም። የኢትዮጵያ መንግስት የግድቡን 30 በመቶ ማጠናቀቁን መናገሩ ይታወሳል።

በካርቱም አካባቢ የሚኖሩ ነዋረዎች ግድቡ አደጋ ቢያጋጥመው ካርቱምን አስራ አምስት ሜትር ድረስ እንደሚያሰጥም በስጋት እየተናገሩ ሲሆን በሳሊኒ ኮንስትራክሽን ላይ ያላቸውን የብቃት ጥርጣሬ እየተናገሩ መሆኑን ወኪላችን ከካርቱም ዘግባል:: ይሁን እንጅ የአልበሽር መንግስት በይፋ ግድቡን መደገፉ ይታወቃል።

የእትዮጵያ መንግስት የጀመረው የግድብ ግንባታ በተለይ በውጭ ባሉ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ተቃውሞ ሲገጥመው ቆይቷል።

ESAT

ገዢው ፓርቲ በጠራቸው ስብሰባዎች ላይ ሁሉ ተቃውሞ ገጠመው

MK
ኢሳት ዜና :- ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ባለፈው ሳምንት በመላ አገሪቱ የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞችን እየሰበሰበ በ2005 የስራ አፈጻጸምና የ2006 ዓም በጀት እቅድ ትግበራ ላይ ሲያወያይ ቢሰነበትም፣ ለኢሳት ሚደርሱት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በሁሉም ቦታዎች ላይ በተደረጉት ስብሰባዎች ከፍተኛ ተቃውሞ አጋጥሞታል።

በአዳማ የተካሄደውን ስብሰባና ተሰብሳቢዎች ያቀረቡዋቸውን ቅሬታዎች ኢሳት ቀደም ብሎ የዘገበ ሲሆን፣ በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር ዞን በአርማጭሆ ወረዳ የነበረው ስብሰባም እንዲሁ በተመሳሳይ ተቃውሞ መጠናቀቁን በውይይቱ የተሳተፉ የመንግስት ሰራተኞች ገልጸዋል።

በውይይቱ ላይ በርካታ አጀንዳዎች የነበሩ ሲሆን፣ ከጸጥታ ጋር በተያያዘ የተነሱት ጉዳዮች ተሰብሰባዊውን በከፍተኛ ሁኔታ አወዛግበዋል።

በ2006 ዓም የጸረ ሰላም ወይም የጥፋት ሀይሎችን ማምከን የሚል በእቅድ እንዲካተት በቀረበው አጀንዳ ላይ ጸረ ሰላም ማን ነው የሚለው ጥያቄ በተሰብሳቢው ተነስቶ የመድረኩ መሪዎች የተለያዩ መልሶችን ሰጥተዋል። የዞኑ የጸጥታ ጉዳዮች ሀላፊ የሆኑት አቶ ወርቁ ሀ/ማርያም ” ነሀሴ ወር ገደማ 30 የሚሆኑ ሰዎች በጎንደር ከተማ ህዝቡን ተነስ በማለት ሲቀሰቅሱ የነበሩ ሰዎች ጸረ ሰላም ሀይሎች ናቸው።” በማለት አንድነት ፓርቲ በጎንደር ያካሄደውን የተቃውሞ ሰልፍ በምሳሌነት አንስተዋል።

ሌላው የሲቪል ሰርቪስ ባለስልጣን የሆኑት አቶ ገዛሀን ተክሌ በበኩላቸው ” የኢትዮጵያ መሬት ለሱዳን ተሰጠ ብሎ መናገር ጸረ ሰላምነት ነው” ሲሉ አብረራርተዋል። ባለስልጣኑ አክለውም ህገመንግስቱን ለመጣስ የሚነሳ ሁሉ ጸረሰላም ተብሎ ይፈረጃል ብለዋል።

የጸጥታ ጉዳዮች ዘርፍ ህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ደግሞ ” ከመድረክ አፈንግጦ መውጣትና ሳያስፈቅዱ መናገር፣ ሳያስፈቅዱ ጽሁፍ መጻፍና ማሰራጨት፣ ሳያስፈቅዱ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ፣ በጥፋት መልእክተኝነት ያስፈርጃል ሲል ገልጸዋል።

አቶ ፈንታ የተባሉ ባለስልጣንም እንዲሁ ” የጎንደርን መሬት ኢህአዴግ አሳልፎ እየሰጠ ነው ” ብሎ መናገር ጸረ-ሰላም ተግባር ነው በማለት የራሳቸውን ትርጉም አቅርበዋል።

ስለ ጸረ ሰላም ሀይሎች፣ አክራሪነትና ሽብረተኝነት ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ ትምህርት እንዲሰጠጥ በቀረበው ሀሳብ ላይ ደግሞ በስብሰባው የተሳተፉ ተቃውሞአቸውን ገልዋል። ተሳታፊዎቹ ከ15 ዓመት በታች ያሉ ህጻናትን ስለ ሽብረተኝነት፣ አክራሪነትና ጸረሰላም ሀይሎች ማስተማር በህጻናቱ ላይ የስነልቦና ጫና ይፈጥራል በማለት ተከራክረዋል።

ሌላው አወዛጋቢ የነበረው ነጥብ ” ኢህአዴግ የ2006 እቅድን ተቋሞችን በድርጅት አባላት በመሙላት እናሳካለን በማለት ያቀረበው ” ሲሆን፣ ተሰብሳቢዎቹ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ሁሉ በድርጅት አባላት ከሞላችሁ የተቃዋሚ ድርጅት አባላትን ምን ልታደርጉዋቸው ነው?” በማለት ጥያቄ አንስተዋል።

ለሱዳን ተላልፎ የተሰጠውን መሬት በተመለከተ የአካባቢው ሰራተኞች የሁለቱን አገሮች ድንበሮች ጠንቅቀው የሚያውቁ በመሆኑ በኢህአዴግ የቀረበውን ማስጠንቀቂያ አልተቀበሉትም።

ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰልፍ ላይቀጥል ይችላል አሉ

5
ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚያደርጓቸው የተቃውሞ ሰልፎች ተደጋጋሚና መንግስት አቋም የያዘባቸውን ጉዳዮች የሚያነሱ እንደሆኑ የጠቆሙት ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ፤ መንግስት ለእያንዳንዱ ሰልፍ ጥበቃ ማድረግ ስለማይችል ሰልፎቹ በተለመደው መልኩ ላይቀጥሉ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ ትናንት በጽ/ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች የራሳቸው የፓርቲዎቹ ሳይሆኑ የሌሎች ሃይሎች እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡

ፓርቲዎቹ ሰልፍ ማካሄድ ህገመንግስታዊ መብታቸው መሆኑን የጠቀሱት ጠ/ሚኒስትሩ፤ መንግስት በተደጋጋሚ ጥበቃ ሲያደርግ ቢቆይም፣ በሰልፎቹ የሚነሱት ጥያቄዎች ፋይዳ ቢስ ከመሆናቸውና ከፓርቲዎቹ ብዛት አንፃር መንግስት በቀጣይ ለሰልፎች ጥበቃ ለማድረግ የሚቸገርበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ መንግስት በተደጋጋሚ ምላሽ የሰጠባቸውን ጥያቄዎች መላልሰው የሚያቀርቡት በመንግስት ላይ ጫና በመፍጠር አቋሙን ለማስቀየር በማሰብ ሊሆን ይችላል ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ይሄ ግን በፍፁም የማይሳካ ሃሳብ ነው ብለዋል፡፡ “ግንቦት ሰባት” በቅርቡ መንግስትን ለመጣል ወታደራዊ እርምጃ እንደሚወስድ በይፋ መግለፁን በተመለከተ ተጠይቀው ሲመልሱም፣ የፓርቲው አመራሮችና ደጋፊዎች ተጨባጭ ያልሆነ ህልም ውስጥ ሆነው የተናገሩት ነገር እንደሆነና ከህልማቸው ሲነቁ እውነታውን እንደሚገነዘቡት ጠ/ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ኢህአዴግ ውስጥ መከፋፈልና የሃይል መጠባበቅ አለ የሚለውን መረጃ በተመለከተም “ይህ የአንዳንድ አፍራሽ ሃይሎች ከንቱ ምኞትና ተጨባጭ ያልሆነ አሉባልታ ነው” ሲሉ አጣጥለውታል፡፡

ኢትዮጵያ፤ ከሶማልያ ወታደሮችዋን እንደማታስወጣ ገለፀች

ll
ኢትዮጵያ በሶማልያ ያሰማራችዉን ጦር እንደማታስወጣ የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ አስታወቁ። ጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ኢትዮጵያ የናይሮቢዉን ጥቃት ተከትሎ ጦርዋን ከሶማልያ የምታስወጣበት ምንም ምክንያት እንደሌላት እና አሸባብን ባላት አቅም ሁሉ እስከ መጨረሻዉ እንደምትዋጋ ተናግረዋል። አልሸባብ ለአካባቢዉ አገሮች አደገኛ መሆኑን የገለፁት የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚኒስቴር፤ አካባቢዉ ላይ ያለዉ ስጋት እስካልተወገደ ድረስ ኢትዮጵያ የአፍሪቃዉን ሕብረት እና የሶማልያን ወታደሮች በሶማልያ ዉስጥ እንደምትደግፍ ተናግረዋል።
በሶማልያ የሚገኙት የእኛ የፀጥታ ጥበቃ ወታደሮች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ፤ አልሸባብ ከአካባቢዉ እስካልተወገደ በሶማሊያ የአፍሪቃ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል AMISOMን እና የሶማልያ ፀጥታ ሃይላትን መርዳታቸዉን ይቀጥላሉ ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም በጋዜጣዊ መግለጫቸዉ ኢትዮጵያ በሶማልያ በቂ ወታደሮች እንዳልዋት ቢያስታዉቁም፤ በቁጥር ምን ያህል ወታደሮች እንዳሏት ግን ከመግለፅ ተቆጥበዋል።
Source/ http://www.dw.de.com

Post Navigation