addisnews

I'm standing for real freedom. I regard freedom of expression as the primary right without which one can not have a proper functioning democracy.

Archive for the day “October 27, 2013”

አስደሳች ዜና: የ 21 ዓመቷ ከሚላት መሃዲ በዛሬው እለት የጋብቻ ስነ ስርዓቷን ፈፅማለች።

AAA33
ከጥቂት አመታት በፊት በደረሰባት ከፍተኛ የአሲድ ጥቃት ጉዳት ደርሶባት የነበረው እና የህዝብ መነጋገሪያ ሆና የቆየችው ከሚላት መሀዲ በሼህ መሀመድ ሁሴን አላሙዲን ድጋፍ በከፍተኛ ወጪ በፈረንሳይ ሀገር የፕላስቲክ ሰርጀሪ ሲደረግላት ቆይታ በዛሬው እለት የጋብቻ ስነ ስርዓቷን ፈፅማለች።
እንኳን ለዚህ አበቃሽ! እግዚአብሄር አምላክ መጪውን ዘመን የጤና፣የደስታ እና የስኬት ያደርግልሽ ዘንድ ከልብ እንመኛለን።
መልካም ጋብቻ!
አዲሱ ዎንድወሰን

የዓረና የማእከላዊ ኮሚቴ አባል ቶርቸር ተደረገ

cccጓዶች የዉቅሮ ስብሰባ ሪፖርት ሳላቀርብ ጠፋሁ። የውቅሮ ከተማ የዓረና ቅስቀሳና የህወሓቶች ምላሽ የሚገርም ነበር። እኛ በደንብ ቀሰቀስን። የዉቅሮ ህዝብ የህወሓትን አገዛዝ እንዳንገሸገሸው ተረዳን።

የኛ ቅስቀሳ ሲጠናቀቅ ህወሓቶች የራስቸው ቅስቀሳ ጀመሩ። ‘የመለስ ራእይ…’ እያሉ እንደተለመደው መዘመር ጀመሩ። (በሚቀጥለው ምርጫ የሚጠቀሙት ቅስቀሳ ‘የመለስ ራእይ’ የሚል መሆኑ ከወዲሁ ማወቅ ችለናል)። ወደ ማታ አከባቢም ቤት ለቤት እየተዘዋወሩ ህዝብ በዓረና ስብሰባ እንዳይሳተፍ፣ እያንዳንዱን ወላጅ ልጆቹ ወደ ስብሰባው እንዳይሄዱ መምከር እንዳለበት ካልሆነ ግን መንግስት እንደካደ ይቆጠርና በመንግስት እርምጃ እንደሚወሰድበት ያስፈራሩት ገቡ።

ቅዳሜ ጠዋት (የስብሰባው ቀን) ሁሉም የዉቅሮ ከተማ አስተዳደር ሰራተኞች የስብሰባው አደራሽ በር ላይ ተገኝተው ወደ ስብሰባው የሚገባ ሰው መከልከል ጀመሩ። የነሱ መከልከል ያልበገረው ሰው ደግሞ ፎቶ ማንሳት ጀመሩ። የቀበሌ ሰራተኞች ህዝብ የቀበሌያቸው ሰው መቆጣጠር ያዙ።

ሲገርመን እኛ ደግሞ እነዚህ ህዝብ የሚቆጣጠሩ ሰዎች ፎቶ ማንሳት ጀመርን። (ካድሬዎቹ ፎቶ እንዳናነሳቸው ይፈሩ ነበር)። አንዱ ሲከለክል አይቼው ፎቶ አነሳሁት። ተናዶ ወደኔ እየሮጠ መጣ። ‘ለምን ያለፍቃዴ ፎቶ ታነሳኛለህ?’ አለኝ። ‘አንተስ ለምን ህዝብ ያለፍቃዱ በስበሰባ እንዳይሳተፍ ታደርጋለህ?’ አልኩት። ‘እኔኮ ፀጥታ የማስከብር ፖሊስ ነኝ’ ብሎ መታወቅያውን አሳየኝ። ይገርማል ። ስሙ ተክላይ ይባላል። የዉቅሮ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ነው። ‘ታድያ ፖሊስ ከሆንክ ለምን ፎቶ መነሳቱ አስፈራህ? ሕጋዊ ስራ እየሰራህ ከሆነ ለምን ትፈራለህ?’ አልኩት። ለመግባት የመጣ ሰው የኛ ንትርክ ለመስማት ከበበን። ፖሊስ አዛዡ (ሲቪል የለበሰ ነው) ‘ዞር በሉ’ ብሉ በተናቸው።

እንዲህ እንዲህ እያለ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ሆነ (ስብሰባው መጀመር የነበረብት 2:30 ነበር)። እኛ በገቡ ሰዎች ስብሰባውን ለመጀመር ወደ አደራሹ ገባን። ከጭቅጭቁ በኋላ ዞምቢዎቹ ሰው በቀጥታ ከመከልከል ወደ በዝምታ መከታተልና በቪድዮ ካሜራ መቅረፅ ተሸጋገሩ።

ስበሰባው ተጀመረ። ህወሓቶች ገብተን ተሰብሳቢውን እንቀርፃለን አሉ። በስሰባው የነበሩ ‘ወጣቶች ህወሓቶች እኛን ለመጉዳት ነው የሚቀርፁት፤ ስለዚህ አስወጡልን’ አሉን። ፖሊስ እንዲወጡ አደረገ። ካድሬዎቹ ከፖሊስ ተጋጩ። ካድሬዎቹና የኛ ሦስት ሰዎች እየተከራከሩ ፖሊስ ጣብያ ዋሉ።

እንዲህ ሁኖ ሰብሰባው በሦስት ሰዓት ተጀምሮ በስምንት ሰዓት በጥሩ መንፈስ ተጠናቀቀ። የህዝብ ብዛት ግን አነስተኛ ነበር። በነበረው መንፈስ መሰረት በሺዎች የሚቆጠር ህዝብ ጠብቀን ነበር (ካድሬዎቹ ባይከለክሉት ማለት ነው)። የመጣ ግን በመቶዎች የሚቆጠር ነበር። እንዲህ ሁኖም ጥሩ ነው። መልእክታችን በሁሉ ቦታ ደርሷል። ያልሰማ የለም ማለት ይቻላል።

ህወሓቶች ፈሪዎች ናቸው። አቶ ገብሩ አስራት ‘ኢህአዴጎች በግለሰብ አስተያየት የሚደነግጡ ናቸው’ ብሎ ነበር። እዉነት ነው። ህወሓቶች ደንግጠው የዉቅሮ ከተማ በየካቲት 11 እንኳ የማይደረግ ቅስቀሳ ጀምረዋል። ዛሬ እሁድ ህዝብ ለሰለማዊ ሰልፍ እንዲወጣ አስገድደው ሰልፍ ጠርተው ነበር። ሰለማዊ ሰልፍ አይፈቀድም እያሉ ራሳቸው ሰለማዊ ሰልፍ ይጠራሉ። በጣም መደንገጣቸው መበስበሳቸው ያሳያል።

ሰብሰባው አጠናቀን ወደ መቐለ ጉዞ ጀመርን። ስብሰባው ይመሩ ከነበሩ የዓረና አመራር አባላት አንዱ የዉቅሮ ከተማ (አጉላዕ) ተወላጅ የሆነና በ2002ዓም ዓረና ወክሎ የፓርላማ ተወዳዳሪ የነበረ መምህር ይልማ ኩኖም ነበር። እኛ ወደ መቐለ ጉዞ ስንጀምር እሱ ቤተሰቡ ለመጠየቅ ዉቅሮ ቀረ።

የህወሓት ፖሊሶች ተከታትለው ያዙት። ስልኩን ነጠቁት። በፖሊስ መኪና ወደ መቐለ ይዘዉት መጥተው ቶርቸው ሲፈፅሙበት አደሩ። አለን የሚሉት የመግረፍት እርምጃ ካደረሱበት በኋላ አሁን ለቀቁት። መምህር ይኩኖ የዓረና ፓርቲ የማእከላዊ ኮሚቴ አባልና የዉቅሮ ከተማ ተወዳዳሪያችን ነው። ለ24 ሰዓት ቶርቸር የሚፈፅሙ አምባገነኖች ያልታገልን ለማን ልንታገል ነው? የሚፈፅሙት ቶርቸር ደርጋዉያን ይፈፅሙት ከነበረ የከፋ ነው።

It is so!!!

ፈስ አጣርቶ የሚያስቀር ውስጥሱሪ በአሜሪካ እጅግ ተፈላጊ ሆኗል

Image

በእንግሊዝ የተፈበረከው ፈስ የሚያጣራ ውስጥሱሪ በአሜሪካውያን ዘንድ በከፍተኛ ሁኔታ ተፈላጊነቱ እየመጣ መምጣቱ ተሰምቷል፡፡ የአምራች ኩባንያ አፈቀላጤ የሆኑት ሲናገሩ “ከአጠቃላይ ሽያጫችን ውስጥ በአሜሪካውያን የሚገዛው እጅግ ከፍተኛውን ቁጥር የያዘ ነው” ብለዋል፡፡

 

ታዋቂው የውስጥሱሪ አምራች ሽሬዲስ በቅርቡ ፈስ አጣርቶ በማስቀረት እንዳይሸት የሚያደርግ ውስጥሱሪ ለወንዶችና ለሴቶች ለገበያ ማቅረቡ ከተሰማ በኋላ ሽያጩ በ400% አድጓል፡፡

 

ኩባንያው እንደሚለው በውስጥሱሪው የውስጠኛ ክፍል ከካርቦን የተሰራ ዞርፍሌክስ የሚባል ጨርቅ የተሰፋ ሲሆን ይህም አማካይ የሽታ መጠን ያላቸውን የፈስ ዓይነቶችን 200 ጊዜ ያህል እንዳይሸቱ የማድረግ ችሎታ እንዳለው አፈቀላጤዋ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

 

ሲቀጥሉም “ይህ የውስጥሱሪ ለሁሉም የሚያስፈልግ ነው፤ ምክንያቱም ሁሉም ሰው ይፈሳል” በማለት የኩባንያቸውን ምርት አስተዋውቀዋል፡፡

 

በኩባንያው የተሰጠው መረጃ እንደሚያመለክተው የወንዶቹ ውስጥሱሪ ዋጋ ከ39 እስከ 45 ዶላር ሲሆን የሴቶቹ ደግሞ ከ31 እስከ 34 ዶላር መሆኑን ጠቁሟል፡፡

 

የዋጋው መጠን ከጾታ አንጻር የበርካታውን ተጠቃሚ አመላካች ሆኖ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ (ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ)

 

“መጽሐፈ ቅዳሴ” ወደ ኦሮምኛ ተተረጎመ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን “መጽሐፈ ቅዳሴ” ወደ ኦሮምኛ ቋንቋ ተተረጎመ፡፡ ለብዙ ዘመናት “መጽሐፈ ቅዳሴ”ን በግእዝ እና በአማርኛ ስትጠቀምበት የቆየችው ቤተክርስትያኗ፤መፅሃፉን በኦሮምኛ ማስተርጎም የጀመረችው በ1999 ዓ.ም እንደሆነ ታውቋል፡፡ የመጽሐፉ መተርጎም በኦሮሚያ ክልል ላሉ አብያተ ክርስትያናት በኦሮምኛ ለመቀደስ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡ የቤተክርስትያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ እያካሄደ ባለው የጥቅምት ምልዐተ ጉባዔው ትኩረት ከሰጣቸው ዋና አጀንዳዎቹ አንዱ ስብከተ ወንጌልን ማዳረስ እንደሆነ የገለፁት ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ የመጽሐፉ ሕትመት እንዲቀላጠፍ ትዕዛዝ እንዳስተላለፉም ለማወቅ ተችሏል፡፡ “መጫፈ ቂዳሴ” በሚል ርዕስ የተተረጎመው የኦሮምኛ መጽሐፉ፤በቅርቡ ዝግጅቱን የተቀላቀሉትን ብፁዕ አቡነ ዮሴፍን ጨምሮ፣ በርካታ ጳጳሳት ተሳትፈውበታል፡፡ መጽሐፉ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት እየታተመ ሲሆን በዚህ ሳምንት ከተጠናቀቀ በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ መዝጊያ ላይ ሊመረቅ እንደሚችል ታውቋል፡፡
12
http://addisadmassnews.com/

Post Navigation