addisnews

I'm standing for real freedom. I regard freedom of expression as the primary right without which one can not have a proper functioning democracy.

ሰበር ዜና በአሁኑ ሰዓት የሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ በታጠቁ ፌደራል ፖሊሶች ተከቧል

mmm
በአሁኑ ሰዓት የሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ በታጠቁ ፌደራል ፖሊሶች ተከቧል
በፓርቲው ጽ/ቤት ውስጥ ወደ 100 የሚጠጉ አባላት የሚገኙ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ወደ 60 የሚሆኔ ከባድ መሳሪያ የታጠቁ የፌደራል ፖሊስ በግቢው ውስጥ ይገኛል ማንም መውጣትም ሆነ መግባት አይችልም፡፡ ያለውን ሁኔታ እየተከታተልን እንገልጽላችኋለን፡
ፓርቲው ከሰላሳ ደቂቃዎች በፊት ባደረሰን መረጃ፤ የሰማያዊ ፓርቲ ፅ/ቤት ከባድ መሳሪያ በታጠቁ ፖሊሶች ተከቧል፡፡ ወደ መቶ የሚጠጉ አባላት በፅ/ቤቱ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የሚፈጠረውን እየተከታተልን እንነግራችኋለን ያለን ቢሆንም ከአስራ አምስት ደቂቃ ቆይታ በኋላ ደግሞ ይህንን መግለጫ አውጥቷል፡፡
ትግላችን የህግ የበላይነትን ወደ ማስከበር ተሸጋግሯል!
ሰማያዊ ፓርቲ ግንቦት 25 ቀን 2005 ዓ.ም. ባካሄደው ታላቅ ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ ለመንግሥት ያቀረብናቸው ጥያቄዎች መልስ ባለማግኘታቸው ለሕዝብ ቃል በገባነው መሠረት በድጋሚ ተቃውሞ ሰልፍ አቅዶ አስፈላጊውን እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡ ለዚህም ሥራ መሳካት ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ነሐሴ 13 ቀን 2005 ዓ.ም. በደብዳቤ ያሳወቀ ሲሆን፣ መጀመሪያ ባቀረብነው ደብዳቤ ላይ ያልተካተቱ ጉዳዮችን እንድናካትት ነሐሴ 15 ቀን 2005 ዓ.ም. በተፃፈልን ደብዳቤ ተጠይቀን አስፈላጊውን መልስ አሟልተን ነሐሴ 17 ቀን 2005 ዓ.ም. በተፃፈ ደብዳቤ አሳውቀናል፡፡
በአዋጁ በግልፅ እንደተደነገገው ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ህገ መንግሥታዊ መብት እንደሆነና ማንም ሊከለክለን እንደማይችል በማያሻማ መንገድ ተገልጿል፡፡ ሰልፉን የማሳወቁ ዓላማ የጥበቃ አገልግሎትና አንዳንድ አስተዳደራዊ ድጋፎችን ለማግኘት ነው፡፡ በዚህ አሰራር ውስጥ መንግሥት የጥበቃና የቦታ ችግር ካለ ሰልፉን ለሌላ ጊዜና ቦታ እንዲያደርግ ለሚመለከተው አካል ደብዳቤ በደረሰው በ24 ሰዓት ውስጥ በፅሑፍ መልስ ይሰጣል የሚል ድንጋጌ አለ፡፡ ነገር ግን በመንግሥት በኩል ላቀረብነው የመብት ጥያቄ ምላሽ መሰጠት ሲገባው እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ የመንግሥት መዋቅር ሙሉ በሙሉ በመጠቀምና ዜጐችን አስገድዶ ሰልፍ እንዲወጡ በማስፈረም ሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ በጠራበት ቀንና ቦታ ሌላ ሰልፍ በተደራቢ በሃይማኖት መቻቻል ስም ህገ መንግሥቱን በመጣስ የሃይማኖት ተቋማትን ለራሱ የድርጅት ፖለቲካ መጠቀሚያና የሰማያዊ ፓርቲን ህጋዊ እንቅስቃሴ ለመግታት እየተጠቀመበት ነው፡፡ ይህ አሰራር እንዲስተካከል መንግሥትን በመግለጫ ብንጠይቅም የተሰጠን ምላሽ ግን በሚያሳዝን ሁኔታ የሀገሪቱን ህገ መንግሥትና የሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን ሙሉ በሙሉ በመጣስ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዲኤታ እንዲሁም ሰልፍ ጠሩ በተባሉ አካላት ግልፅ የሆነና የተቀነባበረ ህገ ወጥ ሴራ ሆኗል፡፡
ስለሆነም በነገው ዕለት ነሐሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም. የምናደርገው ሰላማዊ ሰልፍ ከዚህ ቀደም ያቀረብናቸው ጥያቄዎቻችን እንዲመለሱ ለመንግሥት ጥያቄ ማቅረብ ከመሆን አልፎ የህግ የበላይነትን ወደ ማስከበር አድጓል፡፡ በመሆኑም በመንግሥት የሚደረገው ዓይን ባወጣ ሁኔታ ህግን የመጨፍለቅ ተግባር እንዲቆም ለምናደርገው ትግል የኢትዮጵያ ሕዝብና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ከጐናችን እንዲቆም ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ምንጊዜም የተባበረ የሕዝብ ትግል ያሸንፋል!
ነሐሴ 25 ቀን 2005 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

Single Post Navigation

Leave a comment